ኢራን ለአሜሪካና ለእስራኤል ይሰልል ነበር ያለችውን ዜጋዋን በሞት ቀጣች

ታትሟል

ኢራን ለአሜሪካው ሲአይኤና ለእስራኤሉ ሞሳድ የስለላ ድርጅቶች ሲሰራ አግኝቼዋለሁ ያለችውን ግለሰብ በሞት ቀጣች።

ማሐመድ ሙሳቪ-ማጂድ የተባለው ግለሰብ የኢራን ኃይሎች ሶሪያ ውስጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴና ከወራት በፊት በአሜሪካ የአየር ጥቃት የተገደሉትን የአገሪቱ አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ቃሲም ሶሊማኒን በመሰለልና መረጃ በማቀበል ነው የተከሰሰው።

ኢራን ባለፈው ሳምንት የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቷ ሠራተኛ የሆነን አንድ ግለሰብ የአገሪቱን የሚሳኤል ጦር መሣሪያዎች ዝርዝር ምስጢርን ለአሜሪካ አቀብሏል በሚል በሞት ቀጥታ ነበር።

የኢራን ፍትሕ ተቋም እንዳስታወቀው በማጂድ ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ ተግባራዊ የሆነው ዛሬ ሰኞ ጠዋት "በቀረበበት የስለላ ወንጀል አገሩ ላይ በፈጸመው ክህደት ሳቢያ" ቅጣቱ ተግባራዊ እንደሆነ አመልክቷል።

የሞት ቅጣቱ የተፈጸመበት ግለሰብ ቀደም ሲል አስተርጓሚ የነበረ ሲሆን "በተለያዩ የደኅንነት አካባቢዎች፣ በተለይ ደግሞ በአገሪቱ የጦር ኃይሎችና የኩድስ ኃይሎች በሚባሉት ላይ፣ እንዲሁም የተገደሉት ጄነራል የት እንዳሉ በመጠቆም" የስለላ ተግባር መፈጸሙ ተገልጾ ነበር።

ማጂድ ለፈጸመው የስለላ ሥራ ከሲአይኤና ከሞሳድ ገንዘብ በመቀበልም ተከሶ ነበር ተብሏል።

የፍትሕ መስሪያ ቤቱ እንዳለው ግለሰቡ የተያዘው ከሁለት ዓመት በፊት መሆኑና ከጄነራሉ ግድያ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት እንደሌለው አመልክቷል።

አንዳንድ የኢራን የዜና ተቋማት እንደዘገቡት ማጂድ በቁጥጥር ስር የዋለው በሌባኖሱ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ ሲሆን ቡድኑ ለኢራን አሳልፎ ሰጥቶታል።

ባለፈው ሐምሌ የኢራን የደኅንነት ሚኒስቴር 17 ሰዎች የአገሪቱን የኑክሌርና ወታደራዊ ዘርፍ መረጃን በመሰብሰብ ለአሜሪካ በማቀበል ተግባር ላይ ተገኝተው መያዛቸውን አሳውቆ ነበር። ጨምሮም ከመካከላቸው የተወሰኑት በሞት መቀጣታቸውን ቢገልጽም ማንነታቸውን ይፋ አላደረገም።

የአሜሪካው ፕሬዝድናት ዶናልድ ትራምፕ ግን ኢራን በአገራቸው ላይ ያቀረበቸውን የስለላ ውንጃለ "ሙሉ ለሙሉ ውሸት" ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።