ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጥያቄን ያጫረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጉብኝት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፤ በኤርትራ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ሳዋ በመባል የሚታወቀውን የኤርትራ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል መጎብኘታቸው ተገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከኤርትራው ፕረዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በመሆን ሳዋ ሲደርሱ፤ ለምርቃታቸው ልምምድ ሲያደርጉ የነበሩ የ33ኛው ዙር የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት ሰልጣኞች ወታደራዊ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሳዋ ማሰልጠኛ ማዕከል በአውሮጳውያኑ በ1994 የተቋቋመ ሲሆን፤ ባለፉት 26 ዓመታት የኤርትራ ዋና ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፤ ቀደም ሲል ወደ ኤርትራ በተደጋጋሚ ያቀኑ ቢሆንም ሳዋን ሲጎበኙ ይህ ለመጀመርያ ጊዜያቸው ነው።
ከዚህ ባሻገርም ይህንን ብዙ ተባለለትን ወታደራዊ መሰልጠኛ የሌላ አገር መሪ በይፋ ሲጎበኝ የተለመደ አይደለም፤ በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ ናቸው።
የኤርትራው የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል፤ መሪዎቹ ሳዋን የጎበኙት "እግረ-መንገዳቸውን' እንደሆነ በትዊተር ገጻቸው ላይ አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በኤርትራ በቆዩባቸው ሁለት ቀናት፤ የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል።
ቅዳሜ፤ በአገሪቱ ደቡባዊ ዞን የሚገኘውን የ 'ገርገራ' ግድብን በመዘዋወር በአካባቢው ያለውን የመስኖ እርሻ መጎብኘታቸውን የአገሪቱ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
እሁድ ጠዋት ደግሞ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በጋሽ ባርካ ግዛት የሚገኙትን እርሻዎችንና የ 'ከርከበት' ግድብን ተመልክተዋል።
የኤርትራው ፕረዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፤ በተዳጋገሚ እየተገናኙ ውይይቶችን ያካሄዱ ቢሆንም፤ "በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ" ከሚል መግለጫ የዘለለ ዝርዝር መረጃ ከየትኛውም መንግሥት እስካሁን ተሰጥቶ አያውቅም።
በተመሳሳይም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ለሥራ ጉብኝት ወደ አሥመራ ያቀኑት ከፕሬዝደንት ኢሳያስ ጋር በሁለቱ አገራት ጉዳዮችና ቀጠናዊ ትብብሮችን በማጠናከር ላይ የተኮረ ውይይት እንደሚያካሂዱ የኤርትራው ማስታወቂያ ሚንስትር በትዊተር ካሰፈሩት መልእክት ውጪ የተባለ ነገር የለም።
የፖለቲካ ተንታኞች፤ ሁለቱም መሪዎች በሁለት ዋና ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ ነው የሚል ግምታቸውን ሲያስቀምጡ ቆይተዋል።
የመጀመሪያው በአገራቱ በቅርብ ያደረጉትን ጉብኝት በመጥቀስ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ፕረዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ይፋዊ ያልሆነ የማሸማገል ሚናን እየተጫወቱ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።
ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ፕረዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ብዙ ያልተባለለትንና መቋጫ ያላገኘውን የድንበር ጉዳይ ፍጻሜ ለመስጠት ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ ከዚሁ ጋር ያለውን ፖለቲካዊ ጉዳይንም እንደሚነጋገሩበት ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
የኤርትራው ፕሬዝደንት የካቲት ወር ላይ ከአገራቸው ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወኑ ባሉት ፖለቲካዊ ክስተቶች ላይ "እጃችንን አጣምረን ቁጭ አንልም" ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለው ወዳጅነት እየጠነከረ ለመሆኑ እንደማሳያ ይቀርባል።
በተለይ ከትግራይ ክልል እና ከክልሉ ገዢ ፓርቲ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ አሁን በህወሓትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ ብልጽግና መካከል ያለው አለመግባባትና እየጠነከረ የመጣው መወነጃጀል የድንበሩን ጉዳይ መፍትሄ ለመስጠት አመቺ ጊዜ አይመስልም።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫቸው 'ፖለቲካዊ ጫናዎች' እየደረሱብን ነው በማለት አሁን ፓርቲያቸው ያለበትን ሁኔታ አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ከዚህ በፊት "ወደ ምርጫ ከገባችሁ ትቀጠቀጣላችሁ" የሚሉ ዛቻዎች እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ምርጫውን ለማደናቀፍና ክልሉ ላይ ጫና ለመፍጠር "በውህደት እየሰሩ ነው" ያሏቸውን ኃይሎች በግልጽ ከስሰዋል።
በዚህም መሰረት ከክልላቸው አንጻር ተባብረውብናል ያሏቸውን ኃይሎች "ሻዕቢያ አለ፤ ብልጽግና አለ፤ ባንዳዎችም አሉ" በማለት የሦስት ወገን ጫና እንዳለ አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ሌሎች የኤርትራ ባለስልጣናት በተለያዩ ጊዜያት በይፋ እንደሚናገሩት ለህወሓት በጎ አመለካከት እንደሌላቸው ግልጽ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በህወሓት በዋነኝነት ሲዘወር የነበረው ኢህአዴግ ከስሞ ብልጽግና ሲመሰረት ከጥምረቱ እራሱን ካገለለ በኋላ በማዕከላዊው መንግሥት ውስጥ የነበረው ሚና ከመዳከሙ በላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል።
ስለዚህም በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለው የጠበቀ ወዳጅነት ያለውን ስጋት ያጎላዋል።
ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አህመድ ለሥራ ጉብኝት ወደ አሥመራ ያቀኑት ከፕሬዝደንት ኢሳያስ ጋር በሁለቱ አገራት ጉዳዮችና ቀጠናዊ ትብብሮችን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት ለማካሄድ እንደነበረ የማስታወቂያ ሚንስትሩ የማነ ገ/ መስቀል አስታውቀው ነበር።
ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ ወደ አሥመራ ያቀኑት ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እና አሁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ከፍተኛ ባለስልጣንና ቀደም ሲል በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከነበሩት ከአቶ ሬድዋን ሁሴን ጋር ነበር።