እነ ቢልጌትስ የመረጃ መንታፊዎች ኢላማ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Twitter

ቢሊየኖሮቹ ኤሎን መስክ፣ ጄፍ ቤዞስ እና ቢል ጌትስ በመረጃ መንታፊዎች በትዊተር ላይ በተደረገ የቢትኮይን ማጭበርበር ትኩረት ውስጥ ከገቡ አሜሪካውያን ባለሀብቶች መካከል ናቸው።
የባራክ ኦባማ፣ ጆ ባይደን እና ካንያ ዌስት ይፋዊ አካውንቶችም በክሪፕቶከረንሲ እንዲለግሱ ጠይቀዋል።
"ሁሉም ሰው እንድለግስ ይጠይቀኛል" የሚለው የ ጌትስ አካውንት ነው። " 1,000 ዶላር ልከህልኛል 2,000 ዶላር መልሼ እልክልሃለሁ"
ይህ ከተፈጠረ በኋላ " በትዊተር በጣም ከባዱ ቀን ነው። ይህ በመከሰቱ በጣም አዝነናል" ያሉት የትዊተር አለቃ ጃክ ዶርሲ ናቸው።
አክለውም " ምርመራ አድርገን የተፈጠረው ነገር ምን እንደሆነ በሚገባ ስንረዳ እናሳውቃለን" ብለዋል ዶርሲ።
ቀደም ብሎ፣ ትዊትር ሰማያዊ ምልክት ያላቸውን የተረጋገጡ የትዊተር አካውንቶች በአንድ ላይ መልእክት እንዳይልኩ በማድረግ እርምጃ ወስዶ ነበር።
የይለፍ ቃል መቀየር አልተቻለም እንዲሁም የተወሰኑ አካውንቶችም እንዳይሰሩ ተደርጎ ነበር።
በኋላ ላይ የተረጋገጠ አካውንት ያላቸው ተጠቃሚዎች ትዊት ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ትዊተር ግን አሁንም ለማስተካከል እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 1

ዲሚትሪ አልፔሮቪች ክራውድ ስትራይክ የተሰኘ የሳይበር ሴኩሪቲ ኩባንያ መስራች ሲሆን ለሮይተርስ እንደተናገረው " ይህ በዋናዎቹ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተከሰተ ከባዱ ጠለፋ ነው"
የቴስላ እና ስፔስኤክስ ኃላፊ፣መስክ፣ ይፋዊ የትዊተር ገጽ ላይ በእርሳቸው የዲጂታል አካውንት ላይ "በቀጣዮቹ ሰላሳ ደቂቃዎች ውስጥ" በቢትኮይን ለሚደረግ ማንኛውም ክፍያ እጥፍ እንደሚመልሱ የሚገልጽ መልእክት ሰፍሮ ነበር።
የቢትኮይን ማስፈንጠሪያ አድራሻ ተያይዞ የቀረበው ይህ የትዊተር መልእክት "በኮቪድ-19 ምክንያት ለጋስ መሆን ፈልጌያለሁ" ይላል።
ትዊት የተደረገው መልእክት መጀመሪያ ከተለጠፈ ከደቂቃ በኋላ ጠፍቷል።

የፎቶው ባለመብት, Twitter

ነገር ግን ከመስክ አካውንት የሚመጡ መልእክቶች ቢጠፉም ሌላ መልእክት ከዚያም ሶስተኛ መልእክት ተለጥፏል።
ራፐሩ ካንያ ዌስትና ሚስቱ ኪም ካርዳሺያን፣ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፣ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ጆ ባይደን እና የሚዲያ ቢሊየነሩ ማይክ ብሎምበርግ እንደ ኡበርና አፕል ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎችም በመረጃ መንታፊዎች ተጠቅተዋል።
የባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ትዊተር "በሚቀጥሉት ጥቂት ደቂቃ ውስጥ ደንብ በመተላለፍ ምክንያት አካውንቱ እንደማይሰራ እንዲሁም ተያያዥ ትዊቶችም እንደሚሰረዙ" መግለፁን የሚጠቅስ መልእክት ሰፍሮ ነበር ብለዋል።
የቢልጌትስ ቃል አቀባይም ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል፡ " ይህ ትዊተር ከገጠሙት ትልቅ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑ ነው።" ብለዋል።
የተወሰኑ የተጠለፉና ትዊቶች የተደረገባቸው ተጠቃሚዎች በአንቶኒ ኤልያስ ስም ወደ ተመዘገበ እና cryptoforhealth.com ወደተሰኘ ድረ ገጽ የሚመራ ሲሆን ይህ ደግሞ የተመዘገበው ደግሞ በሳይበር ደህንነት ላይ ጥቃት በሚፈጽም ድርጅት mkworth5@gmail.com በተሰኘ የኢሜል አድራሻ ነው።
ክሪፕቶ ፎር ሄልዝ የኢኒስታግራም ገጽም እንዳለው የተመዘገበ ሲሆን መረጃ ለመመንተፍም ይገለገልበታል።
የዚህ የኢንስታግራም ገጽ ፕሮፋይል ስር የተቀመጠው መግለጫ "እኛ ነን" የሚል ሲሆን የሚስቅ ኢሞጂ ፊት አብሮት አለ።
የኢንስታግራም ገፁ ላይም " የበጎ አድራጎት ጥቃት ነው፤ ገንዘብዎ ወደ ትክክለኛው ቦታ ያመራል" የሚል መልእክት ሰፍሯል።

የፎቶው ባለመብት, Instagram

ይህ "ቢትኮይኖን በእጥፍ ያሳድጉ" የሚል ማጭበርበር በትዊተር ላይ ለዓመታት በተደጋጋሚ የተከሰተ ሲሆን ነገር ግን የአሁኑ በርካታ ታዋቂ ሰዎችን ማጥቃቱ ለየት ያደርገዋል።
በአንድ ላይ በርካታ ታዋቂ ሰዎች ለጥቃት መጋለጣቸው ችግሩ ከትዊተር ከራሱ እንደሆነም ያሳያል ተብሏል።
የመጀመሪያው ግምት ጠላፊዎቹ በትዊተር በኩል የሚፈልጉትን አካውንቶች ላይ ማዘዝ እንዲችሉ የሚያደርግና የይለፍ ቃሎችን ማለፍ የሚያስችል እድል አግኝተዋል የሚል ነው።
ጥቃት አድራሾቹ ከዚህ የበለጠ ቀውስና ችግር ሊያስከትሉ መቻላቸው በግለሰቦችም ሆነ በድርጅቶች ደህንነት ላይ አደጋ መጋረጣቸው በግልጽ ታይቷል።
ነገር ግን የጥቃት አድራሾች ፍላጎት በቻሉት ፍጥነት ገንዘብ መሰብሰብ እንዲሁም "ያገኙትን ነጥቆ" መሮጥ መሆኑ ተስተውሏል።
ጥቃት አድራሾቹ የቢትኮይን አካውንት ከፍተው ገንዘብ በማስቀመጥ አካውንታቸውን ህጋዊ ለማስመሰል የሚሰሩ ሲሆን በዚህኛው ማጭበርበር ምን ያህል ገንዘብ እንዳገኙ ይፋ የተደረገ መረጃ የለም።
ገንዘቡ የገባበትን ተከትሎ ወንጀለኞቹን ለማደን መሞከርም አዳጋች መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ነገር ግን ተጠቃሚዎችም ሆኑ የሕግ አካላት ግን ትዊተርን ይህ እንዴት ሆነ ብለው መጠየቃቸው አይቀርም።

በ2017 ከመንታ ወንድሙ ጋር በጋራ በቢትኮይን ቢሊየነር መሆኑ የተነገረለት ካሜሮን ዊንክሌቮስ ረቡዕ እለት ሰዎች "በማጭበርበር" ላይ እንዳይሳተፉ የሚጠይቅ ማስጠንቀቂያ ትዊት አድርጎ ነበር።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 2















