በመላ ኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከሰተ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty
በኢትዮጵያ ውስጥ የኩፍኝ ወረርሽኝ መከሰቱን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ባለፉት አራት ወራት በሁሉም ክልሎች የኩፍኝ ወረርሽኝ ታይቷል ብለዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች የኩፍኝ ወረርሽኝ "የጤና ሚኒስትርንም የፈተነ" እነደሆነ የገልፁት ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ባለፉት አራት ወራት በተለያየ ምክንያት ክትባት መስጠት መቀዛቀዙንም ጠቅሰዋል።
በወረርሽኙ የተጠቁት በአብዛኛው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው ያሉት ሚንስትሯ፤ ከእነዚህም መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ክትባቱን ያልወሰዱ ህጻናት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሁሉም ክልሎች ለወረርሽኙ መከሰት ምክንያቶች ብለው ሚንስትሯ ሲጠቅሱ፤ ከግንዛቤ ማነስም ሆነ ከአገልግሎት ተደራሽነት አንጻር መደበኛ ክትባቶችን አለመውሰድ፣ ክትባት ጀምረው የሚያቋርጡ ህጻናት ከፍተኛ መሆን፣ እንደዚህም ዘጠነኛ ወር ላይ ከሚሰጠው ክትባት በተጨማሪ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ላይ የሚሰጠውን ሁለተኛ ዙር ክትባት አለመውሰድ ለወረርሽኙ መስፋፋት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመከሰቱ የተነሳ በአገር ውስጥ የመደበኛ ህክምና አገልግሎት ፈላጊዎች ቁጥር መቀነሱን የጠቀሱት ሚንስትሯ፤ ይህም ለወረርሽኙ መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል።
የኩፍኝ ክትባት ካለፈው ሳምንት (ከሰኔ 23/2012) ጀምሮ በዘመቻ መልክ በሁሉም ክልሎች መሰጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።
እስካሁን ድረስ 5.1 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት መከተባቸውን የተናገሩ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ክትባቱን መስጠት ያልጀመሩ አካባቢዎች ቢኖሩም በቅርቡ ግን እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።
እድሜያቸው ከዘጠን ወር ጀምሮ ያሉ ህፃናት ከዚህ በፊት ክትባቱን ቢወስዱም ባይወስዱም እንደሚከተቡ ሚኒስትሯ ዶክትር ሊያ ታደሰ ጨምረው ተናግረዋል።














