የኮሮናቫይረስ "መድኃኒቶች" በጥቁር ገበያ እየተቸበቸቡ ነው

ረምደሲቪር

የፎቶው ባለመብት, HETERO

ታትሟል

የቢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኞች ቡድን እንዳረጋገጠው ሁለት ነብስ አድን የኮሮናቫይረስ መድኃኒቶች ሕንድ ውስጥ ጥቁር ገበያ ላይ በውድ ዋጋ እየተቸበቸቡ ነው።

ረምደሲቪር እና ቶሲሊዙማብ የተሰኙት መድኃኒቶች በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የታመሙ ሰዎችን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው። ነገር ግን ጥቁር ገበያው ላይ እጅግ በናረ ዋጋ እየተሸጡ በመሆኑ እጥረት እያጋጠመ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአቢናቭ ሻርማ አጎት ኮቪድ-19 ተገኝቶባቸው ደልሂ ውስጥ የሚገኝ ሆስፒታል ሲገቡ ከፍተኛ ትኩሳትና የትንፋሽ እጥረት እያሰቃያቸው ነበር። ይሄኔ ነው ዶክተሮች ቤተሰቦቹ ሬምደሲቪር እንዲገዛ ያዘዙት።

መደኃኒቱ ሕንድ ውስጥ ለኮሮናቫይረስ በሽተኞች እንዲሰጥ ፈቃድ አግኝቷል።

ነገር ግን አቢናቭ መድኃኒቱን እንዲህ በቀላሉ ሊያገኘው አልቻለም። የአጎቱ ጤና ሁኔታ ደግሞ ከጊዜ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጣ። ከብዙ ሙከራና የስልክ ጥሪዎች በኋላ መድኃኒቱን ሰባት እጥፍ ከፍሎ ማግኘቱን አቢናቭ ይናገራል።

ይህ የአሚናቭ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ሕንዳውያን ታሪክ እየሆነ መጥቷል።

ምንም እንኳ አንዷ ብልቃጥ መድኃኒት ዋጋዋ 5 ሺህ ሩጲ ቢሆንም ጥቁር ገበያ ላይ እስከ 30 ሺህ ሩጲ እና ከዚያ በላይ እየተቸበቸበ እንደሆነ ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።

ረምደሲቪር የተሰኘው መድኃኒት ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣው በኮቪድ የተያዙ ሰዎችን ሕመም መቀነስ በመቻሉ ነው። በጥናት እንደተረጋገጠው መድኃኒቱ የበሽታውን ምልክት ቀናት ከ15 ወደ 11 ዝቅ አድርጎታል።

ምንም እንኳ ባለሙያዎቹ መድኃኒቱ የመጨረሻው ፍቱን መድኃኒት አይደለም ቢሉም ኮሮናቫይረስን የሚገታ መድኃኒት እስካሁን ባለመገኘቱ ዶክተሮች መድኃኒቱ ጥቅም ላይ እንዲውል እያዘዙ ይገኛሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በሕንዷ መዲና ደልሂ እንዲሁም አካባቢዋ የሚኖሩ ሰዎች መድኃኒቱን ለማግኘት በርካታ ሺህ ሩጲዎች መክፈላቸውን ይናገራሉ። አንዳንዶች ዕድሜ ልካቸውን ያጠራቀሙትን ገንዘብ መድኃኒቱ ለመግዛት አውለናል ይላሉ።

መድኃኒቱ በጥቁር ገበያ ዋጋው እንዲህ ንሮ እንዲሸጥ ያደረገው በቂ አቅርቦት ባለመኖሩ ነው።

መቀመጫውን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ጊሊያድ ሳይንስስ የተሰኘው ተቋም ነው ረምደሲቪር የተሰኘውን መድኃኒት ለኢቦላ በሽታ እንዲውል ነው የሰራው። ድርጅቱ አራት የሕንድ ኩባንያዎች መድኃኒቱን እንዲያመርቱ ፈቃድ ሰጥቷል።

ነገር ግን እስካሁን ድረስ መድኃኒቱን ማምረት የጀመረው አንድ ድርጅት ብቻ ነው።

ይህ ድርጅት 20 ሺህ ብልቃጦችን አምርቶ ለገበያ ማቅረቡን አሳውቆ መድኃኒቱ እንዴት የጥቁር ገበያ ነጋዴዎች እጅ ላይ ሊወድቅ እንደቻለ መረጃው የለኝም ሲል ለቢቢሲ አሳውቋል።

ድርጅቱ ምርቶቹን ለሆስፒታሎች አከፋፍያለሁ ቢልም ሆስፒታሎች ምርቱ የለንም እያሉ ነው። መድኃኒት መሸጫ መደብሮችም መድኃኒቱን መደርደሪያቸው ላይ አይታይም።

እጥረት ያጋጠመው ረምደሲቪር ብቻ ሳይሆን ቶሲሊዙምባ የተሰኘው ሕይወት አድን መድኃኒትም ከገበያ እየጠፋ ነው።

ይህ መድኃኒት በኮሮናቫይረስ ተይዘው የሚማቅቁ ሰዎችን ስቃይ በመቀነስ ረገድ ውጤታማ ነው ተብሎለታል። የሕክምና ባለሙያዎች መድኃኒቱ ተጨማሪ ምርመራ ያሻዋል ይላሉ። ነገር ግን በዓለም ዙሪያ በርካታ ሆስፒታሎች መድኃኒቱ በጎ ውጤት እንዳሳየ ይናገራሉ።

ነገር ግን ይህን መድኃኒት በቀላሉ ማገኘት የማይታሰብ ነው። ሕንድ ውስጥ ያሉ በርካታ ሆስፒታሎች መድኃኒቱ ስለሌላቸው የታካሚ ቤተሰቦች ፈልገው እንዲያመጡ ነው የሚያዙት።

የሁለቱም መድኃኒቶች አምራችና አከፋፋይ ድርጅቶች መድኃኒቶቹ እንዴት ጥቁር ገበያው ሊገኙ እንደቻሉ አናውቅም ይላሉ። በመሃሉ ግን በርካታ ቤተሰቦች መድኃኒቱን ለመግዛት ጥሪታቸውን እያሟጠጡ ይገኛሉ።

ኮሮና
Banner