ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች መጨመር ስጋት ፈጥሯል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከእንስሳ ወደ ሰው የሚሻገሩ በሽታዎች እየጨመሩ መሆናቸውንና ለእንስሳቱ ጥበቃ እንዲሁም ተፈጥሮ እንክብካቤ ካልተደረገ የበሽታዎች መተላለፍ እንደሚቀጥል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች አስጠነቀቁ።
ባለሙያዎቹ፤ ኮቪድ-19ን ለመሳሰሉ በሽታዎች መስፋፋት ከእንስሳ የሚገኘው ፕሮቲን ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ፣ ዘላቂ ያልሆነ የግብርና ሥራና የአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታውች ሳቢያ እንደሚሞቱም ተነግሯል።
ከእንስሳት ወደ ሰው ከተላለፉ በሽታዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገረው ኮቪድ-19 በሰዎች ጤናና ህይወት ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በሁለት ዓመት ውስጥ በዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ የዘጠኝ ትሪሊዮን ያህል ዋጋ ያለው ጉዳትን ያስከትላል።
ኢቦላ፣ ዌስት ናይል ቫይረስና ሳርስ ሁሉም ከእንስሳ ወደ ሰው የተሻጋገሩ በሽታዎች ናቸው።
ነገር ግን በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው የሚሸጋገሩት እንዲሁ በቀጥታ ሳይሆን ሌሎች ገፊ ምክንያቶች አሏቸው።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራምና የዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ተቋም በወጣው ሪፖርት መሰረት የመሬት መራቆት፣ የዱር እንስሳትን አላግባብ መጠቀም፣ የማዕድናት ቁፋሮና የአየር ጸባይ ለውጥ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
እነዚህም የሰው ልጅ ከተፈጥሮ አካባቢና ከእንስሳት ጋር ያለውን ግንኙነት በማበላሽት ለችግር እንደሚኣጋልጠው ባለሙያዎች ጠቁመዋል።
"ባለፈው ክፍለ ዘመን ውስጥ የኖቭል ኮሮናቫይረስ ዝርያ የሆኑ ቢያንስ ስድስት ዋነኛ ወረርሽኞች ተከስተው ነበር" ሲሉ የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም ምክትል ዋና ጸሐፊና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንገር አንደርሰን ተናግረዋል።
ጨምረውም "ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊት በነበሩት ባለፉት ሃያ ዓመታት፤ ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታዎች ምክንያት 100 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ደርሷል።"
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከዚህ ባሻገርም "በድሃና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ አንትራክስ፣ የሳንባ በሽታንና የእብድ ውሻ በሽታን በመሳሰሉ ከእንስሳ ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታዎች ሰበብ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች በየዓመቱ ይሞታሉ" ብለዋል።
ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የሥጋ ምርት በ260 በመቶ መጨመሩን የተናገሩት ኃላፊዋ ለዚህም "የእርሻ ሥራዎችና ምረተ ልማቶች ተስፋፍተዋል፣ የዱር እንስሳት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀማችን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሩል" ሲሉ ምክንያቶችን ጠቅሰዋል።
ሪፖርቱ መንግሥታት የበሽታዎቹን መስፋፋት ለመቆጣጠር ማድረግ ያለባቸውን ነገሮችን ጠቁሟል።
"በሳይንስ እንደተረጋገጠው የዱር እንስሳትን ያላግባብ ስንጠቀምና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ውድመት ሲደርስ በቀጣይ ዓመታት በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው በፍጥነት ሲሸጋገሩ ማየታችን አይቀርም" ብለዋል አንደርሰን።
ጨምረውም ወደ ፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል "የተፈጥሮ አካባቢን በአግባቡ መጠበቅ ይኖርብናል" ሲሉም መክረዋል።

















