ታንዛኒያ ወረርሽኙን ወደ መቆጣጠሩ ደርሻለሁ በማለት የለይቶ ማቆያ ማዕከላትን ዘጋች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታንዛኒያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመቀነሱ በለይቶ ማቆያ ማዕከላትነት እኣገለገሉ የነበሩ ስፍራዎችን እየዘጋች መሆኑን ባለስልጣናት አስታወቁ።
አገሪቱ ቫይረሱ ለተገኘባቸው ሰዎች ለይቶ ማቆያነት 85 ማዕከላትን አዘጋጅታ የነበረ ሲሆን የጤና ሚኒስትሩ ኡሚ ምዋሊሙ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ የሚገኙት የግል ማእከላትን ጨምሮ 11 ብቻ ናቸው።
ሚኒስትሯ በሽታው ከታንዛኒያ እየጠፋ እንደሆነ "እግዚአብሔር ይመስገን ኮሮናቫይረስ በአገራችን ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ነው" ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ጨምረውም ምንም እንኳን በሽታው እየጠፋ ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ሊያገረሽ ስለሚችል ሕዝቡ እንዳይዘናጋ መክረዋል።
ሚኒስትሯ ቀደም ሲል ለህሙማን ለይቶ ማቆያነት ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ ማዕከላት በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ የህክምና አገልግሎት እየሰጡ በመሆናቸው ሕዝቡ ወደዚያው በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችል ገልጸዋል።
መንግሥት ወረርሽኙን በተመለከተ መደበኛ መረጃ ስለማያወጣ በአሁኑ ጊዜ በታንዛኒያ በበሽታው የተያዙ እና ለሞት የተዳረጉ ሰዎች አሃዝ አይታወቅም።
በታንዛኒያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ለመጨረሻ ጊዜ የተገለጸው ባለፈው ሰኔ ወር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ ሲሆን በወቅቱም 66 ህሙማን መኖራቸውን ተናግረው ነበር።
በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም የአየር ትራንስፖርትና የቱሪዝም ዘርፉ ተከፍተው ሥራቸውን እያከናወኑ ነው።
የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመከላከል አካላዊ ርቀትን በማስጠበቅና የእጅ መታጠቢያዎችን በማዘጋጀት የስፖርት ውድድሮችም መካሄድ ጀምረዋል።
ታንዛኒያ በሽታውን በመከላከል በኩል ከጎረቤቶቿ የተለየ አካሄድን በመከተሏ ትችት ሲቀርብባት ቆይቷል። መንግሥትም በቸልተኝነትና በሽታውን በምስጢር በመያዝ ይከሰሳል።
በአገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደብ ያልተጣለ ሲሆን ላላ ያለ በሽታውን የመከላከያ እርምጃዎችን በመውሰድ አገሪቱ ዋነኛ ትኩረቷን ያደረገችው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማጠናከር ላይ ነው።














