ከባለፈው ሳምንት ተቃውሞ በኋላ ሱዳን የፖሊስ አዛዦችን ከሥራ አባረረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት ሰፊ ፖለቲካዊ ለውጦችን በመጠየቅ በመላዋ አገሪቱ የተቃውሞ ሰልፎች ከተደረጉ በኋላ የሱዳን የሽግግር መንግሥት ዋናውንና ምክትል የፖሊስ አዦችን ከሥራ አባረረ።
የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት አብደላ ሐምዶክ ናቸው ሁለቱን ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣናት ከሥራቸው እንዲሰናበቱ ያደረጉት ተብሏል።
በዚህም መሰረት የአገሪቱ ፖሊስ ኃይል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አደል ሞሐመድ ባሺር ከኃላፊነታቸው ተነስተው በኢዝ ኤልዲን ሼክ አሊ እንዲተኩ ተደርገዋል።
የሱዳን ካቢኔ በኋላ ላይ ጨምሮ እንዳስታወቀውም የዋና ዳይሬክተሩ ምክትል የነበሩት ኦትማን ሞሐመድ ዩኑስ በፖሊስ ኃይሉ ውስጥ ከነበራቸው ሥልጣን መባረራቸውን ገልጿል።
ባለስልጣናቱ ከኃላፊነታቸው መባረራቸውን እንጂ ስለእርምጃው የተሰጠ ምንም ምክንያት የለም።
ነገር ግን ባለፈው ሳምንት የተቃውሞ በአስር ሺህዎች በሚቆጠሩ ሰዎች የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ባደረጉት ንግግር ለውጦች እንደሚደረጉ ተናግረው ነበር።
ለተቃውሞ የወጡት ሱዳናዊያን የቀድሞው አስተዳደር ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ባለው ጊዜ በተሰሩ የለውጥ ተግባራት ባለመርካታቸው በርካታ ጥያቄዎችን ይዘው ነበር ወደ አደባባይ የወጡት።
ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከስልጣን ተወግደው የሽግግሩ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ በአገሪቱ የሚካሄደው ለውጥ አዝጋሚ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ለ30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሱዳንን የመሩት አል ባሽር ባለፈው ዓመት ለወራት የዘለቀን ተቃውሞ ተከትሎ በወታደሮቻቸው ከስልጣናቸው ተወግደው በእስር ላይ ይገኛሉ።












