ቱርክ የአምነስቲ የመብት ተሟጋቾችን "በሽብርተኝነት" አሰረች

ታነር ኪሊክ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ታነር ኪሊክ ለሦስት ዓመታት በእስር አሳልፏል
ታትሟል

በቱርክ የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅት የቀድሞ ኃላፊ ታነር ኪሊክ፤ ከሽብር ጋር በተያያዘ ክስ 6 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ የቱርክ ፍርድቤት ውሳኔ አስተላለፈ።

ሌላኛው የቀድሞ ከፍተኛ የድርጅቱ ባለሙያ ኢድል ኢስርም በኢስታንቡል ፍርድ ቤት የሁለት ዓመታት እስር ተፈርዶበት ነበር።

ሁለቱ ግለሰቦች ከሦስት ዓመታት በፊት በአገሪቷ አመፅ በቀሰቀሰና በኢስታንቡል አቅራቢያ በተካሄደ በአንድ ሚስጢራዊ ስብሰባ ላይ ተሳትፈው እንደነበር ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

የአምነስቲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው "ተጨባጭ ያልሆነ ክስ" ሲል ድርጊቱን አውግዞታል።

ቃል አቀባዩ አንድሪው ጋርድነር በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ፤ "ፍርዱን ለማስተላለፍ የሚያስችል ምንም ማስረጃ የለም፤ አሁንም በደሉ እንደቀጠለ ነው፤ ሁሉም ነፃ እስኪወጡ ድረስ ተስፋ አንቆርጥም" ብለዋል።

ክሊክ እና ኢሰርም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሲውሉ በአንድ የሰብዓዊ መብት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ከእነዚህ ግለሰቦች በተጨማሪ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች "ሽብርተኛ የሆነውን ድርጅት በመደገፍ" በሚል የሁለት ዓመታት እስር ተፈርዶባቸዋል።

በሌላ በኩል ጀርመናዊውን ፒተር ስቴውድነረ እና ስዊዲናዊውን አሊ ጋራቪን ጨምሮ ሌሎች ሰባት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን በነፃ ተሰናብተዋል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከአራት ዓመታት በፊት የቱርኩን ፕሬዚደንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተደረገ በኋላ ነበር።

የአምነስቲ የቀድሞ ኃላፊ 14 ወራትን በእስር ካሳለፈ በኋላ ከሁለት ዓመታት በፊት በዋስ ተፈትቶ ነበር።

ይሁን እንጅ አሁን ላይ ክስ የተመሰረተበት በአሜሪካ መሠረት ባደረገውና ሙስሊም መሪ በሆኑት ፈቱላህ ጉለን ከሚመራው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ሲሆን እንቅስቃሴው በፕሬዚደንቱ "በሽብር ፈጣሪነቱ" የተፈረጀ ሲሆን ከአራት ዓመታት በፊት ለተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራም ይወነጀላል።