የኒው ዚላንድ ጤና ሚኒስትር "በፈጸሙት ስህተት" ሥራቸውን ለቀቁ

የጤና ሚኒስትር ዴቪድ ክላርክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጤና ሚኒስትር ዴቪድ ክላርክ
ታትሟል

የኒው ዚላንድ ጤና ሚኒስትር መንግሥት ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሰጠው ምላሽ እንዲሁም የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦችን በመጣሳቸው በደረሰባቸው ትችት ሥራቸውን መልቀቃቸው ተገለጸ፡፡

ሚኒስትሩ በርካታ የእንቅስቃሴ ገደቦችን መጣሳቸውን ተከትሎም ከፍተኛ ጫና ደርሶባቸዋል፡፡ ሚያዚያ ወር ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት የመጀመሪያው ሳምንት ቤተሰባቸውን ወደ ባህር ዳርቻ ይዘው በመሄዳቸው ትችት ተሰንዝሮባቸው ነበር፡፡

ከዚህም ባሻገር በተራራ ላይ ብስክሌት ለመጋለብ ገደቡን ጥሰው ወጥተዋል፤ ሆኖም ወደ ባህር ዳርቻዎች ማሽከርከር ገደብ መጣስ መሆን አለመሆኑ ግልጽ አይደለም፡፡

ይሁን እንጅ ሚኒስትር ዴቪድ ክላርክ የተጣለውን የኮሮናቫይረስ ሕግ በመጣስ ከኃላፊነታቸው ዝቅ ተደርገው የነበረ ቢሆንም በኃላፊነታቸው ለመቀጠል ግን መንግሥት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚሰጠውን ምላሽ የሚያውክ ነው ሲሉ አልተቀበሉትም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን ማክሰኞ ዕለት የሚኒስትሩን መልቀቂያ መቀበላቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኒው ዚላንድ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በምታደርገው ትግል በምሳሌነት የምትጠቀስ አገር ናት፡፡

በአገሪቷ እስካሁን 1 ሺህ 528 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 22 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ባለፈው ወር ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተጣሉ ገደቦች ሙሉ በሙሉ ተነስተው የነበረ ሲሆን አገሪቷም ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆኗን አውጃ ነበር፡፡

ይሁን እንጅ አገሪቱ ያላት ድንበርና የለይቶ ማቆያዎች አያያዟ አስተችቷታል፡፡ ሁለት ሰዎች ሳይመረመሩ ቤተሰባቸውን ለመጎብኘት ከለይቶ ማቆያ የወጡ ሲሆን በኋላ ላይ ሌሎች ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ለዚህ በምሳሌነት ቀርቧል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የጤና ሚኒስትሩ ክላርክ ይህንን ውሳኔ በማስተላለፋቸው ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም መልቀቂያ አስገብተው የነበረ ቢሆንም በተከሰተው የወረርሽኙ ቀውስ ሳቢያ በኃላፊነታቸው ቆይተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ የጤና ሚኒስትሩ ሥራቸውን በመልቀቃቸው ተስማምተው "የጤና አመራራችን ለአገሪቱ ሕዝብ በራስ መተማመን ወሳኝ ነው" ብለዋል፡፡

አገሪቱ መስከረም ላይ ምርጫ እስከምታካሂድ ድረስም የትምህርት ሚኒስትሩ ክሪስ ሂፕኪንስ የጤና ሚኒስተር ሆነው እንደሚያገለግሉ ተገልጿል፡፡

ኮሮና
Banner