ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቻይና እንደ ኮሮናቫይረስ የመዛመት እድል ያለው አዲስ ቫይረስ ተገኘ
ዓለምን እያስጨነቀ እንዳለው የዘመኑ ወረርሽኝ ሊዛመት የሚችል አዲስ የጉንፋን ቫይረስ ቻይና ውስጥ መገኘቱ ተነገረ።
ተመራማሪዎች አሳማዎች ላይ አገኘነው ያሉት ይህ ቫይረስ ወረርሽኝ የመሆን አቅም ያለው ነው ብለዋል።
ሳይንቲስቶቹ ቫይረሱ የዋዛ አይደለም፣ ራሱን ያባዛል በቀላሉ ዓለምን የማዳረስም አቅም አለውም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ይህ ቫይረስ አሳሳቢ ባይሆንም ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገ ውጤቱ አደገኛ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ቫይረሱ ወደ ሰዎች ከተዛመተ ሰዎች ይቋቋሙታል ተብሎ አይገመትም።
በናሽናል አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ ላይ ይህንን ቫይረስ በተመለከተ የደረሱበትን ያተሙት ሳይንቲስቶቹ እንደሚሉት ይህን አዲስ ቫይረስ ለመቆጣጠር አሁኑኑ ሥራ መጀመር ይኖርበታል።
በአሳማ እርባታዎች አካባቢ በሚሰሩ ሠራተኞች ላይ አሁኑኑ ጥብቅ ክትትል መደረግ ይኖርበታልም ተብሏል።
ከዚህ ቀደም ለመጨረሻ ጊዜ ወረርሽኝ የሆነው ጉንፋን በ2009 ነበር በሜክሲኮ አካባቢ የተቀሰቀሰው። ከፍተኛ ጥፋት ያደርሳል ተብሎ የነበረው ይህ ስዋይን ጉንፋን እንደተፈራው ሳይሆን የቀረው በሁለት ምክንያት እንደሆነ ይታሰባል።
አንዱ እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ይህን ቫይረስ የመከላከል አቅም በዘመናት ውስጥ ማዳበራቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ስዋይን ፍሉ ከዚያ በፊት ከተቀሰቀሱ የወረርሽኝ ጉንፋኖች ጋር ተመሳሳይነት ስለነበረው ነበር።
አሁን በአሳማዎች ላይ ተገኘ የተባለው ቫይረስ ግን ወደ ሰዎች ከተዛመተ ለማቆም ፈታኝ የሚሆነው ፍጹም አዲስ በመሆኑ ነው ተብሏል።
ፕሮፌሰር ኪን ቾው በእንግሊዝ ኖቲንግሀም ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ ናቸው። እርሳቸው ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት "አሁን ለጊዜው ትኩረታችን ኮሮናቫይረስ ላይ ነው፤ ትክክልም ነው። በዚህ መዘናጋት ውስጥ ግን አዲስ ቫይረስና አዲስ ወረርሽኝ አይኖርም ብለን ማሰብ ይለብንም" ብለዋል።