ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲስ አበባ በታጠቁ ዘራፊዎችና በፖሊስ መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ጉዳት ደረሰ
አዲስ አበባ ውስጥ የታጠቁ ዘራፊዎች በአንድ የውጭ አገር ዜጎች መኖሪያ ላይ ዘረፋ ፈጽመው ለማምለጥ በሞከሩበት ጊዜ ከፖሊስ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ ሌላ አንድ ሰው ቆሰለ።
ፌደራል ፖሊስ እንዳለው ተጥርጣሪዎቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው የአዲስ አበባ ክፍል ውስጥ አካባቢ በሚገኝ አንድ የቻይናዊያን መኖሪያ ቤት ላይ የዘረፋ ወንጀል ፈጽመው ለማምለጥ ሲሞክሩ ነው ፖሊስ ደርሶ ተኩስ የከፈቱት።
ፖሊስ እንዳለው በዘረፋው ላይ ታሳታፊ የነበሩት ሰዎች ቁጥር ስምንት ሲሆን በፍጥጫው ወቅት ከፖሊስ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ነው ጉዳቱ የደረሰው።
ተጠርጣሪዎቹ ከዘረፋው ቀደም ብሎ በፖሊስ ክትትል እየተደረገባቸው እንደነበረ የገለጸው ፌደራል ፖሊስ ወደ ቻይናውያኑ የመኖሪያ ግቢ በመግባት ዘረፋ ፈጽመዋል ብሏል።
ባለው መረጃ መሰረት በአካባቢው የተሰማራው ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ዘረፋውን ፈጽመው ለማምለጥ ሲሞክሩ እጃቸውን እንዲሰጡ በጸጥታ ኃይሎች ተጠይቀው እንደነበር የፖሊስ መግለጫ አመልክቷል።
ነገር ግን የጦር መሳሪያ ታጥቀው የነበሩት ዘራፊዎች ከፖሊስ ለቀረበላቸው ጥሪ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው "ተኩስ በመክፈታቸው " ተገልጿል።
በዚህም ሳቢያ ከፖሊስ ጋር በመታኮስ ከወንጀሉ አካባቢ ሊያመልጡ ከሞከሩ ሁለት ግለሰቦች መካከል አንዱ ሲገደል ሌላኛው ቆስሎ ሆስፒታል መግባቱንና ቀሪዎቹ ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ፖሊስ አረጋግጧል።
ፖሊስ ጨምሮም ተጠርጣሪዎቹ ግለሰቦቹ ከዚህ ቀደምም የተለያዩ የጸጥታ ኃይሎችን የደንብ ልብሶች በመልበስ እና በጦር መሳሪያ በመታገዝ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም በተለያዩ ስፍራዎች የወንጀል ድርጊቶችን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ገልጿል።
ዛሬ ቀትር ላይ በተፈጸመው በዚህ የተኩስ ልውውጥ በተፈጠረው ስጋት ለሰዓታት በአካባቢው ይካሄዱ በነበሩ እንቅስቃሴዎች ተገትተው መቆየታቸውን በስፍራው ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ፖሊስ ዘረፋው በተፈጸመበት መኖሪያ ውስጥ ባሉ የውጪ አገር ሰዎች ላይም ሆነ በተኩስ ልውውጡ ወቅት በፖሊስ ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የገለጸው ነገር የለም።