በጆርጅ ፍሎይድ ሞት የተሳለቀው ግዙፍ ኩባንያ ተሸጠ

ታትሟል

ከሳምንታት በፊት በአንድ ነጭ ፖሊስ በግፍ ስለተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ምንም የሃዘን ስሜት የለኝም ብለው የነበሩ ግለሰብ ኩባንያ ተሸጠ።

ክሮስፊት በዓለም ደረጃ ግዙፍ የስፖርት እቃዎች አምራችና አከፋፋይ ነው፡፡

ባለፈው ወር የጥቁር አሜሪካዊውን የጆርጅ ፍሎይድን በነጭ ፖሊስ መገደል ተከትሎ የድርጅቱ ባለቤት "በጥቁር ሞት ማዘን የለብንም" ዓይነት ይዘት ያለው ንግግር መናገራቸው ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥረ ነበር።

ይህን ተከትሎ እውቅ አትሌቶች፣ ሸሪክ የስፖርት እቃ አምራቾችና የድርጅቱ ደንበኞች ከክሮስፊት ጋር የሥራ ውላቸውን ማቋረጥ ጀምረው ነበር።

ተቃውሞ የበረታባቸው የክሮስፊት ሥራ አስፈጻሚና ባለቤት ግሬግ ግላስማን ኃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውና ጡረታ መውጣታቸው ይታወሳል።

ሰሞኑን ደግሞ ድርጅቱ መሸጡ ተሰምቷል።

አዲሱ የኩባንያው ባለቤት ኤሪክ ሮዛ ድርጅቱን ከገባበት ማጥ መልሶ ለማውጣት ብርቱ ሥራ ይጠብቀናል ብለዋል።

የክሮስፊት ስፖርት እቃዎች አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ ሀብቱ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ነው።

ድርጅቱ በትንሹ ከ13 ሺህ የሰውነት ማጎልመሻ ማዕከላት ጋር የሚሰራ ሲሆን በ158 አገራት ውስጥ ቅርንጫፎች አሉት።

አዲሱ የድርጅቱ ባለቤት ሚስተር ሮዛ ቀድሞ የኦራክል ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ።

"ባለፉት ሳምንታት በሆነው ነገር ቅር የተሰኙብን ብዙ ናቸው፤ እኔ ማለት የምፈልገው ነገር ግልጽና አጭር ነው፤ ዘረኝነት አስቀያሚ ነው። በአዲሱ ክሮስፊት ዘረኝነት ቦታ የለውም" ብለዋል ሚስተር ሮዛ።

የቀድሞው የድርጅቱ ባለቤት ሚስተር ግላስጎ በትዊተር ሰሌዳቸው "ኮቪድ 19" የሚለውን "ፍሎይድ-19" በሚል ቀይረው በጥቁር አሜሪካዊው ሞት ለመሳለቅ ሞክረው ነበር።

ክሮስፊት በጸረ ዘረኝነት ትግሉ ምነው ዝምታን መረጠ ተብለው በንግድ ሽሪካቸው ተጠይቀው የነበሩት ሚስተር ግላስኮው ጠያቂውን ሰው "ተምታቶብሀል" ብለው ሲተቹት ነበር።

ከዚህም አልፎ ሚስተር ግላስኮው የጂም ባለቤቶችና የንግድ ሸሪኮቻቸውን በዙም ቴክኖሎጂ ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት "እኛ በክሮስፊት ኩባንያው ውስጥ በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ጭራሽ ሐዘን አልገባንም። እኔም ሆንኩ የድርጅቱ ሠራተኞች በክስተቱ አላዘንንም፤ ምን በወጣን?" ብለው ተናግረው ነበር።

ይህ ንግግራቸው ሾልኮ ለሚዲያዎች ከደረሰ ወዲህ ከዚሁ ኩባንያ ጋር የንግድ፣ የማስታወቂያና ሌላ ዓይነት ሽርክና ያላቸው ሁሉም ከድርጅቱ ጋር የሥራ ውል ማቋረጣቸውን ይፋ ሲያደርጉ ሰንብተዋል።