በቻይና ነዳጅ የጫነ ተሸከርካሪ ፈንድቶ 19 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

በቻይና ደቡብ ምስራቅ አካባቢ ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ ፈንድቶ የ19 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ170 በላይ ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

ተሸከርካሪው አደጋው ያጋጠመው ቅዳሜ ዕለት የተፈጥሮ ነዳጅ ጭኖ በዠጂያንግ ግዛት ፈጣን መንገድ ላይ እየተጓዘ ሳለ ነበር፡፡

በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቁ ምስሎችም በአካባቢው ፍርስራሽ እና ጭስ እንዲሁም የተሸከርካሪውን ቅሪተ አካል አሳይተዋል፡፡

ፍንዳታው በመጀመሪያ በዌንሊንግ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ በሊያንግሻን መንደር የደረሰ ሲሆን ፤ ሁለተኛው ፍንዳታ ደግሞ ተሸከርካሪው በመንገድ ዳር ላይ ከሚገኝ አንድ ፋብሪካ ጋር ከተጋጨ በኋላ ነበር ያጋጠመው፡፡

የዌንሊንግ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ዡ ሚንግሊያን፤ ከ2ሺህ 600 በላይ የነፍስ አድን ሰራተኞች በቦታው ላይ ተሰማርተው የሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ እየተረባረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአደጋውን ምክንያት በማጣራት ላይ መሆናቸውንም ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል፡፡

እንደ 'ቾንጊንግ ዴይሊ' የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ከሆነ የተሽከርካሪው ባለንብረት ድርጅት ከዚህ ቀደም የጤናና የደህንነት ደንቦችን በመጣስ አስራ አንድ ጊዜ ተቀጥቷል፡፡

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ቻይና ሰፋፊ ፈጣን መንገዶችን የገነባች ሲሆን ይህም የትራፊክ አደጋ ቁጥሩ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ የመንገድ ደህንነትም የአገሪቷ ትልቅ ስጋት መሆኑን ቀጥሏል፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ በየዓመቱ ከ200 ሺህ በላይ ቻይናዊያን በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡