በናይጄሪያ 40 የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች የፈጸመው ግለሰብ ተያዘ

በናይጄሪያ ካኖ ግዛት በምትገኝ ከተማ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 40 የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች መፈጸማቸውን ተከትሎ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ።
በሰሜናዊ ናይጀሪያ በምትገኘው ዳንጎራ ከተማ የሚኖሩ አንዲት እናት ግለሰቡን ከልጆቻቸው መኝታ ክፍል ውስጥ እንደያዙት የፖሊስ ቃል አቀባይ አብዱላሂ ሃሩና ተናግረዋል።
ግለሰቡ በጊዜው ለማምለጥ ቢሞክርም ሌሎች ጎረቤቶች ተከታትለው ከያዙት በኋላ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ቃል አቀባዩ አክለዋል።
ፖሊስ እንደሚለው የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎቹ በ80 ዓመት እድሜ አዛውንት እና ከ10 ዓመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ ጭምር የተፈጸሙ ናቸው።
በቅርቡ በናይጄሪያ በርካቶችን ያስቆጣ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፊርማዎች የተሰባሰቡበት እና 'ታክቶናል' [ዊ አር ታይርድ] በሚል በሴቶች ላይ የሚደርሱ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችንና ግድያዎችን የተመለከቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል።
ዳንጎራ በናይጄሪያ ካኖ ግዛት የምትገኝ ከተማ ስትሆን ከካኖ ከተማ በ85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
አካባቢው ከከተማ ወጣ በማለቱም ለፖሊስ ተደራሽነት አመቺ አለመሆኗን በሥፍራው የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ መንሱር አቡበከር ዘግቧል።
የከተማዋ አስተዳዳሪ አህማዱ ያኡ "ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ጥሩ እርምጃ ነው። በዚህ ሰዓት በዳንጎራ የሚገኙ ሰዎች በጣም ደስተኛ ናቸው፤ በተገቢው መንገድ ፍትሕ ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም አጥርን እየዘለሉ ቤታቸው በመግባት ሴቶችን የሚደፍሩ ግለሰቦች መኖራቸውን በመስማታቸው ያለፈውን ዓመት በቤታቸው ውስጥም ሆነው በስጋት እንዳሳለፉ አስረድተዋል።
"አሁን አይናችንን ጨፍነን እንተኛለን" ስትል አንዲት ሴት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ባለፈው ዓመት ናይጄሪያ ውስጥ የተደረገ የአንድ ጥናት ውጤት እንዳመለከተው በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ሦስት ሴቶች አንዷ 25 ዓመት እድሜ እስክትደርስ ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ ጾታዊ ጥቃት ያጋጥማታል።
የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴቶች ቤተሰቦች ሊደርስባቸው የሚችልን መገለልን፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት በማጣትና በሌሎችም ምክንያቶች በናይጄሪያ በርካታ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ወደ ሕግ አይቀርቡም ።












