የበኩር ልጃቸውን ለመረከብ ወረርሽኝ ሳይበግራቸው ግዛት ያቆራረጡት ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ወር አጋማሽ ሕንድ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመቆጣጠር ጥብቅ እንቅስቃሴ ገደብ ጥላ ነበር። አገሪቱ ፀጥ ረጭ ባለችበት በዚያ ወቅት ግን ጨቅላ ልጃቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማየት የጓጉ ጥንዶች ግዛቶች አቆራርጠው ተጉዘዋል።
በሕንድ በየአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች ተሰማርተው ነበር። ጥንዶቹን አስቁመውም ወዴት እንደሚሄዱ ጠይቀዋቸዋል።
“የበኩር ልጃችንን ልናይ እየሄድን ነው” ሲሉ ጥንዶቹ ምላሽ ይሰጣሉ።
በዚህ መልስ ግራ የተጋቡ ፖሊሶች “ምን ማለታችሁ ነው? ልጃችሁ የታለች?” እያሉ ይጠይቋቸው ነበር።
ጥንዶቹ ታሪካቸውን እንዲህ ያካፍላሉ. . .
ልጃቸው የተወለደችው ከሳምንት በፊት ነበር። የጥንዶቹን ልጅ አርግዛ የወለደችው ማህጸኗን ያከራየች ሴት ናት። በእንግሊዘኛው 'ሰሮጌት ማዘር' ትባላለች።
ማህጸኗን አከራይታ የወለደችው ሴት የምትኖረው ጉጅራት ግዛት ውስጥ ነው። የጥንዶቹን ልጆች የተገላገለችውም እዛው ነው። ጥንዶቹ ከሚኖሩበት ባንጋሎር ግዛት ወደ ጉጅራት ያቀኑት የመጀመሪያ ልጃቸውን ከወላዷ ተረክበው ወደ ቤታቸው ለመውሰድ ነበር።
ራከሽ (ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ስሙ ተቀይሯል) የልጅቷ አባት ነው። ልጁ የተወለደችው አናድስ አካንሻ በተባለ ሆስፒታልና የጥናት ምርምር ማዕከል ውስጥ ነው።
በማዕከሉ 28 ልጆች ተወልደዋል። የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት በሕንድ እንቅስቃሴ ስለተገታ ልጆቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሳይቀላቀሉ ለሳምንታት ቆይተዋል።
አስር ህጻናት ተወልደው እስከ 50ኛ ቀናቸው ድረስ ቤተሰቦቻቸው አልወሰዷቸውም ነበር።
የማህጸን ኪራይ
በሕንድ የማህጸን ኪራይ እያደገ መጥቷል። በየዓመቱ 1,500 ልጆች በዚህ መንገድ ይወለዳሉ።
በሕንድ ልጅ አርግዞ መውለድ ለማይችሉ ወይም ለማይፈልጉ ሴቶች ማህጸን የሚያከራዮ ሴቶች ሁነኛ አማራጭ ናቸው። ጥንዶች ይህን አማራጭ በተለያዩ ምክንያቶች ሲመርጡ ይስተዋላሉ። ሕንዳውያን እንዲሁም የሌሎች አገሮች ዜጎችም በዚህ መንገድ ወደ ሕንድ በማቅናት ልጅ ያገኛሉ። ሕንድ “የማህጸን ኪራይ ማዕከል” የምትባለውም ለዚሁ ነው።
በሌላ በኩል ዘርፉ ላይ ተገቢው ቁጥጥር እየተደረገ አይደለም የሚሉ አካላት አሉ። ሕንድ ከሁለት ዓመት በፊት ዘርፉን ለመቆጣጠር ይረዳል ያለችውን ረቂቅ ሕግ አውጥታለች።
በረቂቅ ሕጉ መሠረት ጥንዶች ማህጸን መከራየት የሚችሉት ዘመዳቸው ከሆነች ሴት ነው። ረቂቁ ግን ገና አልፀደቀም።
የጉዞ ፍቃድ የማግኘት ፈተና
ራከሽ 47 ዓመቱ ነው። በአማካሪነት ይሠራል። ባለቤቱ አኒታ ደግሞ 41 ዓመቷ ሲሆን፤ ዲዛይነር ናት።
እአአ 2003 ላይ ትዳር የመሠረቱት ጥንዶች ልጅ ለመውለድ ሲሞክሩ ነበር። አኒታ አምስት ጊዜ አስወርዷታል። በማህጸን አከራይ ልጅ ለመውለድ የወሰኑት ባለፈው ዓመት ነበር።
ከዛም ጉጅራት የምትገኘውን ሴት ተዋወቁ። የራሷ ሁለት ልጆች ያሏት ሲሆን ማህጸኗንም ታከራያለች።
የራከሽና አኒታ ልጅ የተወለደችው ባለፈው ወር መባቻ ላይ ነበር። እንደተወለደች ፎቶዋ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ተልኮላቸዋል።
“የልጃንን ፎቶ ቪድዮ አይተን ባለቤቴ ማልቀስ ጀመረች። በጣም ስሜታዊ ሆነን ነበር” ይላል ራከሽ።
ሕንድ የየብስም ሆነ የአየር ጉዞ አግዳለች። ጥንዶቹ ልጃቸውን ለማየት ቢጓጉም ጉዞ መጀመር ቀላል አልነበረም። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ለመንቀሳቀስ ፍቃድ ለማግኘት ጊዜ ይወስዳል።
“በምርምር የተወለደች ልጅ ወደ ቤት ለመውሰድ ምን ያስቸኩላል? ባለችበት መቆየት ትችላለች አይደል?” ሲሉ ጥንዶቹን የጠየቁ ባለሥልጣኖች ነበሩ።
ልጅቷ የተወለደችበት ሆስፒታል ኃላፊ ዶ/ር ናያና ፔታል፤ ለፍቃድ ሰጪዎቹ ባለሥልጣኖች “ጨቅላዎቹን ለቤተሰቦቻቸው ማስረከብ ስላልቻልን ተቸግረናል” ሲሉ ኢሜል ልከዋል።
በስተመጨረሻ ጥንዶቹ ከሹፌራቸው ጋር የጉዞ ፍቃድ አገኙ።
ጉዞ ወደ በኩር ልጅ. . .
ጉዞው ሁለት ቀን የፈጀ ነበር። ምሽት ላይ ነዳጅ ማደያ እየቆሙ እራት ይበሉ፣ ስልካቸውንም ቻርጅ ያደርጉ ነበር።
ጥንዶቹ በቂ ምግብና አስር ሊትር ውሃ ይዘው ነበር።
“በጣም ይሞቅ ስለነበር መተኛት አልቻልንም። ምን ያህል ጊዜ ፖሊሶች እንዳስቆሙን መቁጠር አቁሜ ነበር። እንድናልፍ ሲፈቅዱልን በፍጥነት አልፈናቸው እንሄድ ነበር” ይላል ራከሽ።
በእያንዳንዱ የፍተሻ ጣቢያ ሙቀታቸው ይለካ ነበር። ስማቸውንና አድራሻቸውን ይሰጣሉ፤ ስለ ልጃቸውም ማብራሪያ ይሰጣሉ። “ሂደቱ አታካች ነበር” ይላል አባትየው።
ጉጅራት ሲደርሱ በግዛቲቱ ብዙ ሰዎች በኮቪድ-19 ስለተያዙ መግባት እንደማይቻል ፓሊሶች ነገሯቸው። በጉጅራት 14,000 ሰዎች በበሽታው ተይዘው 850 ሰዎች ሞተዋል።
ወደ ግዛቲቱ መግባት በሚፈልጉና በተከለከሉ ሰዎች መካከል ግብግብ ተፈጥሮ ነበር። አንድ ፖሊስ የተፈጠረውን ውዝግብ የሚያሳይ ቪድዮ ቀርጿል።
ከተጓዦቹ አንዱ እናቱን ለመቅበር ወደ ደልሂ የሚሄድ ነበር። “እንዴት እናቴ ሞታ ጥቃት ታደርስብኛለህ?” ሲል ከፖሊስ ጋር ሲጣላ ይታያል።
ከአራት ሰዓታት በኋላ ተጓዦቹ ፍቃዳቸውን እያሳዩ እንዲያልፉ ተፈቀደላቸው።
"ጓንታችንን አውልቀን ልጃችንን አቀፍን”
ልጆች የተወለዱበት ማዕከል ቤተሰቦች ለሁለት ሳምንት በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ አድርጓል።
ጥንዶቹ ከለይቶ ማቆያ ከወጡ በኋላ ከተወለደች ሦስት ሳምንት የሆናት የበኩር ልጃቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ በአይነ ሥጋ ማየት ቻሉ።
ክፍላቸውን አጽድተው፣ ጓንትና ጭምብል አድርገውም ነበር የተቀበሏት።
“አኒታ ልጃችንን ስታይ ማልቀስ ጀመረች። ትንሽ ቆይተን ጓንታችንን አውልቀን ልጃችንን አቀፍን” የሚለው ረከሽ ቅጽበቱን እንዲህ ያስታውሳል. . .
“ልጃችንን መሳም እንችላለን ወይ? ብለን ሀኪሙን ስንጠይቅ አትችሉም አለን። ሆኖም የወሰድንላትን ሰማያዊ ቀሚስ አለበስናት። የደስታ ሲቃ ተናንቆኝ ነበር። በስተመጨረሻ ልጃችን በእቅፋችን ገባች። ያን ቅጽበት መቼም ቢሆን አልረሳውም። ስናቅፋት አላለቀሰችም ነበር። ትኩር ብላ አየችን።”
ጥንዶቹ መቼ ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ እርግጠኛ አይደሉም። ሕንድ እንቅስቃሴ ላይ የጣለችውን ገደብ ብታነሳም የየብስና የአየር ጉዞ አልተጀመረም።
ጥንዶቹ እጅ ማጽጃ (ሳኒታይዘር)፣ አስር የጨቅላ ወተት (ፎርሙላ)፣ ዳይፐር ገዝተው ወደ ቤታቸው የሚያደርጉትን ጉዞ ለመጀመር ተዘጋጅተዋል።
የቀራቸው መኪና ማግኘት ብቻ ነው።
“ትዕግስት የሚፈታተን ጉዞ ነው ያደረግነው። ልጅ የማግኘት ጥረትም በውጣ ውረድ የተሞላ ነው። ልጄን ለማየት ያለፍኩት ፈተና ቀላል አልነበረም። ቢሆንም ፈተናው ትዕግስተኛ እናት አድርጎኛል” ትላለች አኒታ።














