"ቶኒ አለን ባይኖር አፍሮቢት አይፈጠርም" የተባለለት ሙዚቀኛ አረፈ

ቶኒ አለን

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

ታትሟል

የአፍሮቢት ሙዚቃን በመፍጠር ረገድ ፈር ቀዳጅ ሚና የሚይዘው ናይጄሪያው ሙዚቀኛና ከበሮ ተጫዋች ቶኒ አለን በ79 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።

ሙዚቀኛው የሞተው ፓሪስ እንደሆነም ማኔጀሩ አስረድቷል።

"የአሟሟቱን ምክንያት አናውቅም" በማለት ማኔጀሩ ኤሪክ ትሮሴት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተናገረ ሲሆን፤ ከኮሮናቫይረስ ጋር እንደማይያዝም አሳውቋል።

ቶኒ አለን በአፍሪካ ሙዚቃ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ላለው ናይጄሪያዊው ሙዚቀኛ ፌላ ኩቲ ታዋቂ ባንድም የሙዚቃ ዳይሬክተር እንዲሁም ከበሮ ተጫዋች ነበር።

ፌላ ኩቲ በአንድ ወቅትም ስለ ቶኒ አለን የሙዚቃ ሊቅነት ሲመሰክር "ቶኒ አለን ባይኖር ኖሮ፤ አፍሮቢትም አይኖርም" ብሏል።

በአገሩ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገራት የሙዚቃ ችሎታው የተደነቀለት ቶኒ አለን "በአለም ላይ ካሉ ከበሮ ተጫዋቾችም ታላቁ" የሚሉ ሙገሳዎችንም አግኝቷል።

የቶኒ አለን የሙዚቃ ጉዞን እንዲሁም የህይወት ታሪኩን እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጣር 2013 በተሰራው ዘጋቢ ፊልም "ማስተር ድራመር ኦፍ አፍሮቢት" ብዙዎች ተመልክተውታል።

አፍሮ ቢት ድንበር፣ እድሜ፣ ዘር፣ ቀለም ሳይገድበው አለምን ማገናኘት የቻለ የሙዚቃ አይነት ሲሆን የምዕራብ አፍሪካውያንን ፉጂ፣ ጃዝን እንዲሁም ፈንክ የሙዚቃ ስልቶችንም ያጣመረ ነው።

በሌጎስ የተወለደው ሙዚቀኛው ከበሮ መጫወትን የተማረው በራሱ ሲሆን፣ በአስራ ስምንቱ አመቱ ነው።

ለዚህ ደግሞ አሜሪካዊውን የጃዝ ከበሮ ተጫዋች ማክስ ሮች ቴክኒኮችን በማየትና በመድገም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገለት በአንድ ወቅት ተናግሯል።

ቶኒ ከፌላ ኩቲ ጋር የተዋወቁት በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ1964 ሲሆን 'ጀንትልማን'፣ 'ዞምቢ' የመሳሰሉ በርካታ አልበሞችን አብረው ሰርተዋል።

ቶኒ በጎርጎሳውያኑ 1979 ከፌላ ጋር በተፈጠረ አለመግባባትም ከባንዱ ወጥቷል። ፌላም ያንን ክፍተት ለመሙላት አራት ከበሮ ተጫዋቾች መቅጠር ነበረበት።

ከሶስት አስርት አመታት በፊትም ቶኒ መኖሪያውን ለንደን አድርጎ የነበረ ሲሆን በመቀጠልም ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በፓሪስ ነበር የሚኖረው።