በናይጄሪያ የነዳጅ ቦቴ ፍንዳታ 15 ሰዎችን ገደለ

የናይጄሪያ የምጣኔ ኃብት ማዕከል በሆነችው የሌጎስ ከተማ ትናንት በአንድ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በደረሰ ቃጠሎ ቢያንስ 15 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል። ከሟቾቹ በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ አያሌ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱም ታውቋል።
የናይጄሪያ የፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን አደጋውን አስመልክቶ በሰጠው ምላሽ ጉዳቱ የደረሰው አንድ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ተሽከርካሪ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ሲሊንደርን በመግጨቱ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
ቃጠሎው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦው ላይም በከፊል ጉዳት ማድረሱ የታወቀ ሲሆን በዚህም ምክንያት የአገሪቱ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ የነዳጅ ቱቦዉን ለመዝጋት ተገዷል።
የናይጄሪያ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኢብራሂም ፋሪንሎየ እንዳስታወቁት በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳት ባለፈ ቢያንስ 50 የሚሆኑ ሕንጻዎች በቃጠሎው ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
በአቅራቢያው የሚገኘውና እስከ 250 ተማሪዎች እንደሚማሩበት የሚገመተው ትምህርት ቤትም በቃጠሎው ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል ነው።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአሁኑ ወቅት ከአካባቢው ፍርስራሾችን በማንሳት ላይ ናቸው።
አንድ የናይጄሪያ ቀይ መስቀል ከፍተኛ ኃላፊ እንዳረጋገጡት ደግሞ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል የተወሰኑት ጉዳት ደርሶባቸዋል።
አቢቦላ አዮ የተባለ የአካባቢው ነዋሪ በሰጠው ምስክርነት መሰረት ቃጠሎውን ቢያንስ 3 ኪሎሜትር ከሚርቀው ቤቱ ሆኖ የተመለከተ ሲሆን እጅግ አስፈሪ እንደነበር ገልጿል።












