አሜሪካ ውስጥ ቤት የሌላቸው ታዳጊ ተማሪዎች ቁጥር ጨመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ውስጥ መኖሪያ የሌላቸው ታዳጊ ተማሪዎች ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ከታየው ከፍ ባለሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አንድ ጥናት አመለከተ።
ቁጥራቸው 1.5 ሚሊዮን ከሚሆኑት ቤት አልባ ታዳጊ ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ ቤታቸውን ካጡ በኋላ ኑሯቸውን የሚገፉት ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር ነው።
በብሔራዊው ቤት አልባ ተማሪዎች ማዕከል የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው 7 በመቶ የሚሆኑት ከትምህርት ቤት መልስ የሚኖሩት ባዷቸውን በተተዉ ህንጻዎችና መኪኖች ውስጥ ነው።
በታዳጊ ታማሪዎች ላይ የሚታየው ቤት አልባነት ምክንያት በአብዛኛው በሥራ አጥነት፣ በመኖሪያ ቤቶች ኪራይ መወደድ፣ በቤት ውስጥ በሚፈጸም ጥቃትና በቅርቡ ደግሞ በዕጽ መጠቀም ሳቢያ ነው።
ታዳጊ ልጆቹ ቋሚ የሆነ አድራሻ ሳይኖራቸው መቅረቱ በትምህርታቸውና በጤናቸው ላይ ከባድ ተጽእኖ እንዳለው ተገልጿል።
ሪፖርቱ እንዳመለከተው ቤት ከሌላቸው ተማሪዎች መካከል ከአንድ ሦስተኛው ያነሱት በበቂ ሁኔታ ማንበብ የሚችሉ ሲሆን በሒሳብና በሳይንስ ትምህርቶች ዝቅተኛ ውጤትን አስመዝግበዋል።
ጥናቱ የተመለከታቸው በአንድ የትምህርት ዘመን ውስጥ በአንድ ወቅት ቤት አልባ ሆነው የነበሩትን ሲሆን ይህም በአሜሪካ ውስጥ በአጠቃላይ ቤት የሌላቸውን ወጣቶች የሚያጠቃልል አይደለም ተብሏል።
በአሜሪካ አጋጥሟል በተባለው የቤት ቀውስ ሳቢያ ቤት አልባነት እያደገ የመጣ ችግር እንደሆነ ይነገራል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሚያገኙት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ገቢያቸውን በቤት ላይ ያውሉታል፤ በርካቶች ደግሞ የእራሳቸው ቤት ለመግዛት አቅሙ እንደሌላቸው ይናገራሉ።
ካሊፎርኒያ ውስጥ የቤት ኪራይ መጨመርና የቤት እጥረት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በቂና አመቺ ባልሆነ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል።
የፋብሪካዎች መዘጋትና ቋሚ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ አለመኖር እየተለዋወጠ ካለው ኢኮኖሚ ጋር ተዳምሮ ወላጆች የቤት ኪራይ መክፈል እንዳይችሉ አድርጓል።
ሁለት ሚሊዮን ሰዎችን ሱሰኛ ያደረገውና እየተስፋፋ የመጣው መድሃኒቶችን እንደ እጽ ቀውስ አንዳንድ ቤተሰቦችን እንዲበተኑ ወይም ልጆች ከወላጆቻቸው እንዲለዩ በማድረግ ምክንያት ሆኗል።
ቤት አልባነትን በቅርበት የሚከታተሉ አብዛኞቹ ባለሙያዎች እንሚሉት ችግሩን ለመቅረፍ መፍትሄ የሚሆነው በርካሽ ቤቶችን ማቅረብና በተለያዩ ችግሮችና በሱስ ለተጠቁ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል።












