በኢራን የእንግሊዝ አምባሳደር በቁጥጥር ስር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በኢራን የመንግስት ኃለፊዎች የዩክሬኑን አውሮፕላን ተኩሰው መጣላቸውን ከገለጹ በኋላ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የእንግሊዝ አምባሳደር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
አምባሳደር ሮብ ማኬይር በኢራን ሀላፊዎች ለሶስት ሰዓታት ተይዘው የቆዩ ሲሆን እንግሊዝ የአምባሳደሩን በቁጥጥር ስር መዋል ''ተገቢ ያልሆነና ዓለማቀፍ ሕግን የጣሰ'' በማለት ገልጻዋለች።
አምባሳደሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት በዩክሬኑ አውሮፕላን አደጋ ለሞቱ ሰዎች በተዘጋጀው የማስታወሻ ሥነ ስርዓት ላይ ነው። ዝግጅቱ ከታሰበለት ዓላማ በማለፍ ወደ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀይሮ ከፖሊስ ጋር ግጭት ተፈጥሮ ነበር።
አምባሳደር ሮብ ማኬይር ሥነ ስርዓቱን ከታደሙ በኋላ ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ ከመመለሳቸው በፊት ጸጉር ቤት ጎራ ባለቡት ወቅት ነበር በፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው።
የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስለጉዳዩ ባወጣው መግለጫ ''ቴህራን ውስጥ ያለምንም ማብራሪያ የአምባሳደሩ በቁጥጥር ስር መዋል ተገቢ ያልሆነና ዓለማቀፍ ሕግን የጣሰ ተግባር ነው'' ብሏል።
አንድ የኢራን የዜና አውታር እንደዘገበው አምባሳደሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት በኢራን ጸረ መንግስት ተቃውሞዎችን አነሳስተዋል በሚል ነው።
የኢራን ጦር ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ የዩክሬኑ የመንገደኞች አውሮፕላን "ሆነ ተብሎ አለመመታቱን" ገልጿል።
በኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተነበበው የጦሩ መግለጫ፤ አውሮፕላኑ በኢራን አብዮታዊ ጥበቃ አቅራቢያ በሚገኙ የደህንነት ሥፍራዎች እየበረረ ስለነበረ ''በሰዎች ስህተት" ተመትቶ ስለመጣሉ ተነግሯል።
በመግለጫው የመንገደኞች አውሮፕላኑ ተመትቶ ለመውደቁ ኃላፊነት የሚወስዱት ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሏል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሮሃኒ በበኩላቸው ''የኢራን ጦር በስህተት አውሮፕላኑን መትቶ ስለመጣሉ ደርሰንበታል፤ ይቅር የማይባል ስህተት ነው የተፈጠረው'' ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩክሬን እና ኢራቅ መንግሥታት አውሮፕላኑ በስህተት በሩሲያ ሰራሽ ሚሳኤል ተመትቶ ስለመውደቁ መረጃው አለን ማለታቸው ይታወሳል።
ምዕራባውያኑ መንግሥታት ይህንን መረጃ በሚያሰራጩበት ወቅት፤ የኢራን ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ኃላፊ አሊ አቤደዛዱህ "አውሮፕላኑ በምዕራብ አቅጣጫ ከአየር ማረፊያ ተነስቶ መብረር ከጀመረ በኋላ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ወደ ቀኝ ዞሮ ተመልሶ ለማረፍ እየመጣ ሳለ ነው የተከሰከሰው" በማለት ማስተባበያ ሰጥተው ነበር።












