በቡሌ ሆራና በሀዋሳ የኒቨርሲቲ የተፈጠረው ምን ነበር?

የፎቶው ባለመብት, Hawasa/ Bule Hora University FB
ትናንት በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተቀሰቀሰ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ሲያልፍ በርካቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው የዩኒቨርሲቲው የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ሰይፉ ለቢቢሲ ገለጹ።
በተያያዘም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ተማሪዎች መካከል ተነሳ በተባለ ግጭት የአንድ ተማሪ ሕይወት አልፏል። በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠረው ምን ነበር?
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ተማሪዎች መካከል ተነሳ በተባለ ግጭት የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አርማየ አሰፋ ገልፀዋል።
ኃላፊዋ እንደገለፁልን እስካነጋገርናቸው ሰዓት ድረስ በዩኒቨርሲቲው ግጭት አለመኖሩን ገልፀው፤ ከትናንት በስቲያ አመሻሹ ላይ ሱራፌል ሳሙኤል የተባለ የአንደኛ ዓመት ተማሪ በተማሪዎች ማደሪያ ኮሪደር ላይ ወድቆ መገኘቱን ተናግረዋል።
"ተማሪው በተገኘ ሰዓት ደም እየፈሰሰው ነበር። ወዲያውኑ ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተወሰደ፤ ነገር ግን በጣም አስጊ ሁኔታ ውስጥ ስለነበር ሕይወቱ ሊተርፍ አልቻለም" ብለዋል።
ተማሪው በስለት የመወጋት አደጋ እንዳጋጠመው የገለፁት ኃላፊዋ፤ ለተጨማሪ ምርመራ አስክሬኑ ወደ ሚንሊክ ሆስፒታል መላኩን በትናንትናው ዕለት ነግረውናል።
ከተማሪው ሞት ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ወደ 44 የሚደርሱ ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አስረድተዋል።
ሟች ተማሪ፤ የእርሱ የዶርም ልጅ ከነበረና አሁን ተጠርጥሮ በተያዘ ተማሪ መካከል የግል ግጭት እንደነበራቸውም ኃላፊዋ አክለዋል።
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ
ያነጋገርነው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በምዕራብ ኦሮሚያ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ወዲህ የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት መቋረጡን በማስመልከት ተማሪዎች ጠዋት 2፡30 አካባቢ ሰልፍ እንደወጡ ይናገራል። እርሱ እንደሚለው ሰልፉ ሰላማዊ ነበር።
ይሁን እንጅ የዩኒቨርሲቲ ግቢ ፖሊሶች "ቀጠቀጡን" ይላል። በዚህም ስምንት ሰዎች በጥይት ሲመቱ የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን ገልፆልናል።
ሕይወቱ ያለፈው ተማሪ በጥይት የተመታው በግቢው 'ዲኤስቲቪ' የሚባል አካባቢ ነው ይላል።
"ተተኩሶብናል፤ የግቢው ፖሊስ መሳሪያ ይዞ ባይረብሽ በሰላም ወጥተን በሰላም እንገባ ነበር" የሚለው ተማሪው፤ በዱላ እና በጥይት ጉዳት የደረሰባቸውም በርካቶች እንደሆኑ ነግሮናል።
ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የዩኒቨርሲቲው የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ሰይፉ፤ በግጭቱ የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን እና አንድ ተማሪ በጥይት እግሩ ላይ ተመትቶ ወደ ሃዋሳ ሆስፒታል መላኩን አረጋግጠዋል።
ተማሪዎቹ በአራቱ የወለጋ ዞኖች ለምን የኢንተርኔትና ስልክ አገልግሎት ተቋረጠ፣ ለምን በኮማንድ ፖስት ሥር ሆነ የሚሉ መፈክሮችን ይዘው እንደነበር አቶ ዳንኤል ገልፀውልናል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ተማሪዎች ሰላማዊ አካሄድ አልነበራቸውም፤ ድንጋይ መወርወር፣ መስታወቶችን መሰባበር ላይ ነበሩ።
ይሁን እንጅ "ተማሪ ላይ አልተተኮሰም ፤ ወደ ላይ ነበር ሲተኮስ የነበረው፤ በተማሪ ጀርባ የገባ እና በተማሪዎች ውስጥ ሆኖ የሚተኩስ አካል እንደነበር ነው የፀጥታ አካላት እየገለፁ ያሉት" ሲሉም ገልፀውልናል።
በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲም እንዲሁ፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ያለውን ችግር በመቃወም ከትናንት በስቲያ ምሽት በተነሳ ግጭት በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። ይህንን ተከትሎ በዩኒቨርሲቲው ግጭት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ነበሩ ባላቸው 77 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው ተማሪዎች ሁለቱ ከትምህርታቸው ሲሰናበቱ፤ 75 ተማሪዎች ደግሞ ለሁለት ዓመታት ያህል ከትምህርታቸው ታግደዋል።
በቅርቡ የጅማ፣ ወሎ፣ ጎንደር እና ድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋት ተሳትፎ ነበራቸው ባሏቸው ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል።
አራቱ ዩኒቨርሲቲዎች እርምጃ የወሰዱት በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ወራት በተከሰቱት ግጭቶች ተሳትፎ ነበራቸው ባሏቸው ከ470 በላይ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች ላይ ነበር።














