ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሊየርና የባለስቲክ ሚሳይል ሙከራዎችን እንደገና እንደምትጀምር አስጠነቀቀች

ታትሟል

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ፒዮንግያንግ አቋርጣው የነበረውን የኒውክሌር ፕሮግራም በአዲስ መልክ እንደምትጀምር አስታወቁ።

ኪም ጆንግ ኡን የኒዩክሌርና ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይል ሙከራቸውን ለመተው የደረሱትን ስምምነት ማጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።

ኪም እንዳሉት ከሆነ፤ በቅርቡ አገራቸው አዲስ ስልታዊ መሳሪያ ታስተዋውቃለች። ይሁን እንጅ አሁንም ለድርድር በራቸው ክፍት እንደሆነ በመግለፅ የሙከራው ሁኔታ በአሜሪካ አመለካከትና ውሳኔ ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።

በኒውክሌር ድርድሩ አሜሪካ አዲስ ሃሳብ ይዛ አለመምጣቷ እንዲሁም ከደቡብ ኮሪያ ጋር የምታካሂደውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ መቀጠሏ ኪም እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረሳቸው ምክንያት ነው ተብሏል።

በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል የነበረው ድርድር በዋሽንግተን የተካሄደ ሲሆን፤ ፒዮንግያንግ የኒዩክሌር ፕሮግራሟን ሙሉ በሙሉ ካልተወች የተጣለባት ማዕቀብ እንደማይነሳ በተደረሰ ስምምነት ነበር የተጠናቀቀው።

ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በርካታ የጦር መሣሪያዎችን የሠራች ሲሆን፤ ይህም አሜሪካ ስምምነት ላይ እንድትደርስ ጫና ለማሳደር የተደረገ ሙከራ እንደሆነ ተቆጥሯል።

ነገር ግን በኒዩክሌር ሙከራዋና አሜሪካ ሊደርስ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ዓለም አቀፋዊ ባሊስቲክ ሚሳይል ለጊዜው ለማቆም መወሰን በዋሽንግተን የተካሄደው ድርድር ዋነኛ አጀንዳ ነበር።

ፒዮንግያንግ ተጨማሪ ሙከራዎች ማድረጉ አሜሪካን ሊያስቆጣ ይችላል በሚልም ከአውሮፓዊያኑ 2017 ጀምሮ እንዲህ ዓይነት ሙከራዎችን አድርጋ አታውቅም።

ፒዮንግያንግ አቅራቢያ በሚገኝ የሰሜን ኮሪያ ማዕከል እየተደረገ ያለን እንቅስቃሴ የሚያሳይና አገሪቱ ሮኬት ለማስወንጨፍ ወይም ሳተላይት ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ እንዳለች የሚጠቁም የሳተላይት ምስል መገኘቱ የሚታወስ ነው።

የተገኘው የሳተላይት ምስል ሰሜን ኮሪያ አብዛኛውን ጊዜ ባለስቲክ ሚሳይሎችና ሮኬቶችን የምትገጣጥምበት የሳኑምዶንግ ማዕከል ሲሆን እዚህ ማዕከል ውስጥ በርካታ እንቅስቃሴ ሲደረግ እንደነበር ከምስሉ መረዳት ተችሎ ነበር።

ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ተገናኝተው የመከሩት ኪምና ዶናልድ በመካከላቸው አንጻራዊ ሰላም ወረደ ሲባል እንደገና እየደፈረሰ ቀጥሏል።