ቻይናዊው ሳይንቲስት በሰው ልጅ ሽል ላይ ባደረገው ሙከራ ታሰረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በዓለማችን የመጀመሪያዎቹ ዘረ መላቸው የተስተካከለ ህጻናትን የፈጠረው ቻይናዊ ሳይንቲስት የሦስት ዓመት እስር ተፈረደበት።
ሳይንቲስቱ ሂ ጂያንኩዊ ለእስር የተዳረገው በሰው ልጅ ሽል ላይ የዘረ መል ማስተካከያ በማድረግ ኤችአይቪን ለመከላከል እንዲችሉ ባካሄደው ሙከራ ነው።
ቅጣቱ የተጣለበት የቻይና መንግሥት በሰው ሽል ላይ የሚደረግ ሙከራን የሚከለክለውን እገዳ በመተላለፉ መሆኑ ተገልጿል።
ተመራማሪው ባለፈው ኅዳር ወር ስላካሄደው ሙከራና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ስለተወለዱ መንታዎች ይፋ ካደረገ በኋላ ከዓለም ዙሪያ ውግዘት ደርሶበት ነበር።
የቻይና ዜና ወኪል ዢንዋ እንደዘገበው ቀደም ሲል ሳይረጋገጥ የቆየ ሦስተኛ ህጻን በተመሳሳይ ጊዜ መወለዱም ተነግሯል።
ጉዋንግዶንግ የተባለው የቻይና ግዛት አስተዳደርም ህጻናቱ በህክምና ክትትል ስር እንዲሆኑ ማድረጉም ተገልጿል።
ሳይንቲስቱ ፈጽሞታል በተባለው ህገወጥ ሳይንስሳዊ ሙከራ ከተፈረደበት የሦስት ዓመታት እስር በተጨማሪ 430 ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣትም ተጥሎበታል።
ብይኑን ያስተላለፈው ፍርድ ቤት ሳይንቲስቱ ሂ ሙከራውን በሚያካሂድበት ወቅት ተባብረውታል በተባሉ ሁለት ሰዎች ላይም ዝቅ ያለ የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል።
ሻንዢ በተባለችው ግዛት ውስጥ የተሰየመው ፍርድ ቤት በውሳኔው ወቅት እንዳለው "ግለሰቦቹ ለግል ጥቅምና ዝና ሲሉ የህክምና ሥርዓትን ጥሰዋል" መባሉን ዢንዋ ዘግቧል።
"ግለሰቦቹ የሳይንሳዊ ምርምርና የህክምና ሥነ ምግባርን ጥሰዋል" ሲል ፍርድ ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።
ሳይንቲስቱ ሂ ከሁለት ዓመት በፊት የሽላቸው ዘረ መል የተስተካከለ መንታ ህጻናት መወለዳቸውን በቪዲዮ ይፋ አድርጎ ነበር።
ሂ ስለሙከራው ሲናገር "ሥራዬ አወዛጋቢ እንደሚሆን እረዳለሁ፤ ነገር ግን ወላጆች ይህንን ቴክኖሎጂ እንደሚፈልጉት አምናለሁ። ስለዚህም የሚሰነዘረውን ትችት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ" ብሏል።
ቪዲዮው ይፋ ከሆነ በኋላ በዓለም ዙሪያና ቻይና ውስጥ ካሉ የሳይንስ ባለሙያዎች በዚህኛው ላይ የቀረበው ውግዘት ከባድና ኀይለኛ ነበር።
የቻይና መንግሥትም ሳይንቲስቱ ላይ ፖሊስ ምርመራ እንዲያደርግበትና እያካሄደ የነበረው የምርምር ሥራም እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበረ።












