ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኬንያዊው ድምጻዊ ባለስልጣናትን በሚተች ዘፈኑ በፖሊስ ተጠራ
'ኪንግ ካካ' የተባለው ኬንያዊ አርቲስት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የለቀቀውን ዘፈኑን ተከትሎ ቃሉን እንዲሰጥ በፖሊስ መጠራቱን በትዊተር ገጹ ላይ አሳወቀ።
ድምጻዊው በአገሪቱ ስላለው ሙስናና አስተዳደራዊ ችግሮችን በተመለከተ ባወጣውና በኬንያዊያን ዘንድ መነጋገሪያ በሆነው አንድ ዘፈኑ ሳቢያ ነው በፖሊስ የተፈለገው ተብሏል።
ድምጻዊው "ዋጂንጋ ኒይኒይ" [ሞኞች ናችሁ] በሚል ርዕስ የለቀቀውን ሙዚቃ ከዩቲዩብና ከሌሎች የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን መድረኮች ላይ እንዲያነሳ ወይም የስም ማጥፋት ክስ እንደሚጠብቀው ሰኞ ዕለት ተነግሮት ነበር።
በሙዚቃው ውስጥ አን ዋይጉሩ የተባሉት የአንድ ግዛት አስተዳዳሪና የቀድሞ ሚኒስትር ስም ተጠቅሷል። በዚህም ምክንያት ባለስልጣኗ ስማቸው መጥፋቱን በመግለጽ ሙዚቀኛው ይቅርታ ጠይቆ ለጥፋቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነቱን በጽሑፍ እንዲገልጽ ጠይቀዋል።
ባለስልጣኗ ጨምረውም በትክክለኛ ስሙ ኬኔዲ ኦምቢማ በመባል የሚጠራው "ኪንግ ካካ" የተጠየቀውን ካላደረገ ረቡዕ ክስ እንደሚመሰርቱበት በጻፉት ደብዳቤ አመልክተዋል።
ይህ በኬንያዊያን ዘንድ መነጋገሪያ የሆነው ሙዚቃ ለሕዝብ የቀረበው ባለፈው ቅዳሜ ሲሆን፤ በሙስና ቅሌት የሚከሰሱ ባለስልጣናትን ስም ይጠቅሳል። በተጨማሪም መራጩ ሕዝብ ግለሰቦቹን ለስልጣን በማብቃቱ ይተቻል።
ዴይሊ ኔሽን የተባለው ታዋቂ ጋዜጣ ሙዚቃው "የአመራር ችግር፣ ሙስና፣ የፖለቲካ ብዝበዛ፣ ሥራ አጥነት፣ የትምህርት ጥራት ችግርን ጨምሮ ከባለፈው ጠቅላላ ምርጫ ወዲህ በአገሪቱ ያሉ ጉዳዮችን ያነሳል" ሲል ዘግቧል።