የጠፋው የቺሊ አውሮፕላን፡ የሰዎች አስክሬን መገኘቱን የአገሪቷ መንግሥት አስታወቀ

ታትሟል

ባለፈው ሰኞ 38 ሰዎችን አሳፍሮ በመጓዝ የነበረው የቺሊው አውሮፕላን ለቀናት ጠፍቶ ከቆየ በኋላ የአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች ነው የተባለ፤ የሞቱ ሰዎች የአካል ክፍል መገኘቱን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ወታደራዊ አውሮፕላኑ ወደ አንታርቲካ በመሄድ ላይ ሳለ ደብዛው ጠፍቶ መቅረቱን ባለሰፈው ሰኞ ነበር የሃገሪቱ የአየር ኃይል ያስታወቀው።

ሲ- 130 ሄርኩለስ የተባለው አውሮፕላን ፑንታ አሬናስ ከተባለው ካምፕ ከተነሳ ከሁለት ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነበር ከኦፕሬተሮች ጋር ግንኙነቱ የተቋረጠው።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩ ሰዎች መካካል 17 ሰራተኞችና 21 ተሳፋሪዎች የሚገኙበት ሲሆን ወደ አንታርክቲካ የተጓዙት የአቅርቦት ድጋፍ ለማድረግ ነበር።

ታዲያ ዛሬ የአውሮፕላኑ ስብርባሪና የሰዎች አስክሬን መገኘቱ ተሰምቷል።

የማጋያነስ ገዥ የሆኑት ጆሴ ፈርናንዴዝ እንዳሉት ለተሳፋሪ ቤተሰቦች የአውሮፕላኑን መገኘት እንዳሳወቁ ገልፀዋል።

ቀደም ብሎ የቺሊ አየር ኃይል የአውሮፕላኑ ስብርባሪ በባህር ላይ ተንሳፎ መገኘቱን አስታውቆ ነበር።

"በጣም የሚያሳዝን አጋጣሚ ነው" ያሉት ገዥ ፈርናንዴዝ፤ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፤ የአውሮፕላኑ ስብርባሪና በአደጋው የሞቱ ሰዎች አስክሬን መገኘቱን ከአየር ኃይሉ ዛሬ መረጃ እንደደረሳቸው ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ የቺሊ አየር ኃይል መረጃውን አስመልክቶ ያለው ነገር የለም።

ፈርናንዴዝ እንዳሉት የአውሮፕላኑ ጎማ፣ የሞተር አካል፣ የአውሮፕላኑ ዋና ክፍል ስብርባሪ በባህሩ ላይ ተንሳፎ ተገኝቷል።

አክለውም ከአውሮፕላኑ እንደወደቁ የተገመቱ የግለሰቦች ቁሳቁሶች መገኘታቸውን ገልፀዋል።

የብራዚል የጦር መርከብ ለእርዳታ ተልካላች። የብራዚል ፕሬዚደንት ጀር ቦልሶናሮ፤ የብራዚል መርከብ የቺሊ አውሮፕላን አካል የሆኑ ስብርባሪዎችን እና የግለሰብ ቁሳቁሶችን መሰብሰቡን በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

አውሮፕላኑ ከቺሊ ደቡባዊ ከተማ ፑንታ አሬና በአንታርክቲካ ወደ ሚገኘው ፕሬዚደንት ኤድዋርዶ ፈሬ ሞንታላቫ ካምፕ እያመራ ነበር።

የቺሊ አየር ኃይል የአውሮፕላኑን የበረራ መስመር የሚያሳይ ካርታ አውጥቶ የነበረ ሲሆን፤ የበረራ ጊዜው እንዳመለከተው ከ1፡04 ደቂቃ በኋላ በፕሬዚደንት ኤድዋርዶ ፍሬ ሞንታላቫ ማረፍ ይጠበቅበት ነበር።

አውሮፕላኑ ከተሰወረ አንስቶ በአየርና በውሃ ላይ ፍለጋዎች ተጧጡፎ ነበር። አርጀንቲና ፣ብራዚል፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኡራጓይ ለፍለጋ የሚረዱ አውሮፕላኖችን የላኩ ሲሆን፤ አሜሪካና እስራኤል ደግሞ የሳተላይት ምስሎችን በመላክ ፍለጋው ላይ ተሳትፈዋል።

ተሳፍረው የነበሩት እነማን ናቸው?

ከተሳፋሪዎቹ መካከል ሦስቱ የቺሊ ወታደሮች ሲሆኑ፤ ሁለቱ ደግሞ በምህንድስናና በኮንስትራክሽን ሙያ ተቀጥረው የሚሠሩ እና በወታደራዊ ካምፑ ለሥራ እያመሩ የነበሩ ሲቪሊያን ናቸው።

እንደኛው ደግሞ ተማሪ ሲሆን ቀሪዎቹ 15 ተጓዦች የአየር ኃይሉ አባላት መሆናቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ አንዲት የ37 ዓመት ክላውዲያ ማነዞ የተባለች ሴት ፎቶግራፍ አንሽም ትገኝ ነበር። ፎቶ አንሽዋ አየር ኃይሉን የተቀላቀለችው በአውሮፓዊያኑ 2008 ነበር። ክላውዲያ በሳተላይትና በአውሮፕላን በመታገዝ ፎቶግራፎችን የማንሳት ፍቅር ነበራት።

ከዚህም በተጨማሪ ሊዩስ እና ጀርሚያስ የተባሉ ወንድማማቾች በአየር ኃይሉ የኤሌክትሪካል ሥራዎችን እንዲያከናወኑ ተቀጥረው በማምራት ላይ ነበሩ።