38 ሰዎችን ያሳፈረው የቺሊ አውሮፕላን የገባበት አልታወቀም

ታትሟል

38 ተሳፋሪዎችን የያዘ አንድ የቺሊ ወታደራዊ አውሮፕላን ወደ አንታርቲካ በመሄድ ላይ ሳለ ደብዛው ጠፍቶ መቅረቱን የኃገሪቱ የአየር ኃይል አስታወቀ።

ሲ- 130 ሄርኩለስ የተባለው የመጓጓዣ አውሮፕላን ፑንታ አሬናስ ከተባለው ካምፕ ከተነሳ ከሁለት ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ኦፐሬተሮች ግንኙነታቸውን ማቋረጣቸው ታውቋል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩ ሰዎች መካካል 17 ሰራተኞችና 21 ተሳፋሪዎች የሚገኙበት ሲሆን ወደ አንታርክቲካ የተጓዙት የአቅርቦት ድጋፍ ለማድረግ ነበር ተብሏል።

የቺሊ የአየር ኃይል እንዳስታወቀው አውሮፕላኑን የመፈለግና ጉዳት ደርሶበትም ከሆነ የሰዎችን ሕይወት ለማዳን የሚደረገው እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ገልጿል።

ኢኤፍኢ የተባለ የሀገሪቱ የዜና ወኪል እንደዘገበው በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች መካከል ሶስቱ ብቻ ምንም አይነት ወታደራዊ ግንኙነት የላቸውም።

የሀገሪቱ ባለስልጣናት ብዙ መረጃ ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን አውሮፕላኑ ግን 'ኪንግ ጆርክ' በሚባለው ደሴት ላይ በሚገኘውና በቀድሞው ፕሬዝዳንት በተሰየመው ኤድዋርዶ ፍሬ ሞንታልቫ ወታደራዊ ካምፕ በረራ ሲያደርግ መጥፋቱን ገልጸዋል።

የቺሊው ፕሬዝዳንት ሴባስቺያን ፒኔራ በበኩላቸው አውሮፕላኑ መጥፋት እጅግ እንዳሳሰባቸውና ሁኔታውን ከሴሪሎስ አየር ኃይል ጣቢያ ሆነው እየተከታሉት እንደሆነ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት አስታውቀዋል።