ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዴልሂው የፋብሪካ ቃጠሎ በርካቶች ሞቱ
በሕንዷ ዋና ከተማ ዴልሂ በፋብሪካ ውስጥ ባጋጠመ ከባድ የእሳት ቃጠሎ ከ 30 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተዘገበ።
ዛሬ ጠዋት ሊነጋጋ ሲል በማዕከላዊ ዴልሂ የተነሳውን ዐእሳት ተከትሎ በርካታ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ወደ ስፍራው በፍጥነት ሲሄዱ ተስተውለዋል።
ብዙ የፋብሪካው ሰራተኞች እሳት አደጋው ሲከሰት በርካታ ተደራራቢ ክፍሎች በነበሩት ፋብሪካው ውስጥ ተኝተው እንደነበር የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ገልጸዋል።
ከእሳቱ ከባድነት አንጻርና ምን ያክል ሰው በፋብሪካው ውስጥ እንደነበረ ስለማይታወቅ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተነግሯል።
የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ አሚት ሻህ አደጋውን '' ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት የቀጠፈ አሳዛኝ ክስተት ነው'' ብለውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በበኩላቸው የእሳት አደጋው እጅግ ዘግናኝ እንደሆነ በመግለጽ ባለስልጣናትና የሚመለከታቸው ሰዎች በሙሉ በአደጋው ቦታ እርዳታ ለማድረግ የቻሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው ብለዋል።
የተቃጠለው ፋብሪካ የሚገኝበት 'አናጅ ማንዲ' የሚባለው ቦታ በከተማዋ ያሉ ትልልቅ የገበያ ቦታዎች መገኛ ሲሆን እጅግ ጠባብ የሆኑት መረማማጃ መንገዶች ደግሞ የሕይወት ማዳን ስራውን ፈታኝ አድርጎታል። እሳቱንም መቆጣጠር አዳጋች ሆኗል።
እስካሁን 56 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት ወስደዋል።
የዴልሂ እሳት አደጋ አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አቱል ጋርግን ጠቅሶ 'ሒንዱስታን ታይምስ' ጋዜጣ እንደጻፈው ሁሉም ተጎጂዎች በከባድ ጭስ ታፍነው ስለነበር እራሳቸውን ስተዋል።
ሌላ የእሳት አደጋ ሰራተኛ ደግሞ ፋብሪካው የትምህርት ቤት ቦርሳዎችን፣ ጠርሙሶችን እና ሌሎች በርካታ ቁሳቁሶችን ለማከማቸት ይውል እንደነበር ገልጿል።
ለበርካታ ህንዳውያን ሞት ምክንያት የሆነው የእሳት አደጋ መነሻው ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።