ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በዋና ዋና የስፖርት ውድድሮች ላይ እንዳትሳተፍ ታገደች
ሩሲያ ለአራት ዓመታት በዋና ዋና ስፖርታዊ ውድድሮች እንዳትሳተፍ በዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች መድሃኒት ኤጀንሲ ታገደች።
በዚህም ምክንያት ሩሲያ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ እንዲሁም በአውሮፓዊያኑ 2022 በኳታር በሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ላይ ሰንደቅ ዓላማዋ እንዲውለበለብም ሆነ ብሔራዊ መዝሙሯ እንዲዘመር አይፈቀድላትም።
ይሁን እንጅ ከአበረታች መድሃኒት ጋር በተያያዘ ክስ የሌለባቸው ስፖርተኞች ገለልተኛ የሆነ ሰንደቅ ዓላማን ወክለው መወዳደር ይችላሉ።
የዓለም ፀረ-አበረታች መድሃኒት ኤጀንሲ [ዋዳ] ዋና ኮሚቴ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው በስዊዘርላንድ ባካሄደው ስብሰባ ላይ ነው።
ውሳኔው የተላለፈው የሩሲያ የፀረ-አበረታች መድሃኒት ኤጀንሲ በአውሮፓዊያኑ ጥር 2019 የተካሄደውን የምርመራ ውጤት ለማሳወቅ ባወጣው መግለጫ ላይ ቅሬታ አለማቅረቡን ተከትሎ ነው።
የተላለፈው ይሄው የምርመራ ውጤት፤ ለኤጀንሲው በ2018 አወዛጋቢ ለነበረው መግለጫው ከሦስት ዓመታት በኋላ በመንግስት የተደገፈው የአበረታች መድሃኒት ቅሌትን ያረጋገጠ ነው።
የኤጀንሲው ፕሬዚደንት ክሬግ ሬዳይ ውሳኔው "ሩሲያ እያጋጠማት ያለውን የአበረታች መድሃኒት ቀውስ ለመግታት የተወሰደ እርምጃ ነው" ብለዋል።
"ሩሲያ የዓለም አቀፉን ፀረ-አበረታች መድሃኒት ማህበረሰብን ለመቀላቀልም ሆነ ችግሩን መስመር ለማስያዝ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ትችላለች፤ ይሁን እንጅ ባለችበት ሁኔታ መቀጠልን መርጣለች" ሲሉም የዓለም የፀረ አበረታች ኤጀንሲ ምክትል ፕሬዚደንት ሊንዳ ሄሌላንድ እገዳው በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።
"በአገሪቷ ላይ የማያፈናፍን ማዕቀብ እንዲጣል እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም የንፁህ ስፖርተኞች ኃላፊነት አለብን" ሲሉም አክለዋል።
ኤጀንሲው እንዳለው የሩሲያ የፀረ-አበረታች ኤጀንሲ እግዱን በተመለከተ ቅሬታውን ለስፖርት የግልግል ዳኝነት [ካስ] ማቅረብ እንደሚችል ገልፆ የ21 ቀናት የጊዜ ገደብ አስቀምጧል።
ሩሲያ በ2014 በሶቺ የተካሄዱት ጨዋታዎች ተከትሎ ከታገደች በኋላ በአውሮፓዊያኑ 2018 በፕዮንግቻንግ የኦሎምፒክ ውድድር ላይ በአጠቃላይ 168 የሚሆኑ ስፖርተኞች አገሪቷን በማይወክሉ ሰንደቅ ዓላማዎች ለመወዳደር ተገደዋል።
በሶቺ በተካሄደው ውድድር ላይ ሩሲያዊያን ስፖርተኞች 33 ሜዳሊያዎችን ያገኙ ሲሆን 13ቱ የወርቅ ሜዳሊያ መሆናቸው ይታወሳል።
ሩሲያ ከ2015 ጀምሮ በሩጫ ውድድር እንዳትሳተፍ መታገዷም ይታወቃል።