ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማድሪድ ውስጥ ስደተኛ ሕፃናት የተጠለሉበት ካምፕ ላይ የእጅ ቦንብ ተወረወረ
በስፔን ማድሪድ የስደተኛ ሕጻናት ማቆያ ካምፕ ማዕከል ላይ ተወርውሮ የነበረው ቦምብ ጉዳት ሳያደርስ ፖሊስ አከሸፈው።
የእጅ ቦምቡ ረቡዕ ጠዋት ማዕከሉ ግቢ ውስጥ ነበር የተወረወረው።
ማዕከሉ ውስጥ የነበሩት ሁሉም ታዳጊዎች እና ሰራተኞች እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ፖሊስ የእጅ ቦምቡን ማክሸፉ ተነግሯል።
በማዕከሉ ውስጥ በብዛት ስደተኛ የሆኑ ወላጅ የሌላቸው ታዳጊዎች ተጠልለው ይኖሩበታል።
የስፔን ባለስልጣናት ጉዳዩን እየመረመሩ ሲሆን፤ ፖሊስ እስካሁን በቁጥጥር ሥር ያዋለው ሰው የለም እንዲሁም ወንጀሉን ለመፈጸም መነሾ ምን እንደሆነ አልታወቀም።
የሃገሪቱ ፖለቲከኞች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና የሰብዓዊ ምበት ተሟጋቾች ጥቃቱን አውግዘዋል።
ይህ የስደተኛ ታዳጊዎች ማቆያ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየተሰነዘሩበት ሲሆን፤ ከሳምንታት በፊትም ወደ ሰላሳ የሚጠጉ ወጣቶች አጥሩን ሰብሮ ለመግባት ሞክረው ነበር።
በማዕከሉ ላይ የደረሰው ተደጋጋሚ ጥቃት በሃገሪቱ ህዝብ መካከል ስደተኞችን በተመለከተ ያለው አመለካከለት ጫፍ መርገጡን እና ጉዳዩ ማህበራዊ ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን ይጠቁማል ተብሏል።
በስፔን የሚገኙ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ይህ መሰል ማዕከል የወንጀል መጠንን ከፍ እንደሚያደርጉ በመጥቀስ ስደተኛ ጠል አቋማቸውን ያንጸባርቃሉ።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በቀጥታ የቴሌቪዥን የፖለቲከኞች ክርክር ላይ የቀኝ ዘመም ቮክስ ፓርቲ መሪው ሳንቲያጎ አብስካል ይህ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚደርስበት ማዕክል ውስጥ የሚኖሩ ታዳጊ ስደተኖች በአከባቢው ለሚስተዋለው ከፍተኛ የወንጀል ቁጥር ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።
"እዛ አካቢቢ ባሉ መንገዶች ላይ ሁል ጊዜ የውጪ ሃገር ታዳጊዎች ብቻቸውን እመለከታለሁ። በመንገድ ላይ የማገኛቸው ሰዎች በዛ አካበቢ የሚኖሩ ሰዎች ጌጣ ጌጦችን እንዳያደርጉ ፖሊስ እንዳስጠነቀቃቸው ይነግሩኛል። ሴት ልጆቻቸውም ሲያመሹ ትንኮሳ እንዳይፈጸምባቸው እንደሚሰጉ ጨምረው ነግረውኛል" ሲሉ የፓርቲው መሪ ሳንቲያጎ አብስካል ተደምጠዋል።