ኡጋንዳ ለተማሪዎች ለመፈተን ተቀጥረው የመጡ 12 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለች

የፎቶው ባለመብት, Daily Monitor Twitter page
ታትሟል
የኡጋንዳ ፖሊስ የአንደኛ ደረጃ ፈተናን ለተማሪዎች ለመፈተን ተቀጥረው የመጡ 12 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ደይሊ ሞኒተር ጋዜጣ ዘግቧል።
ትምህርት ቤቱ የሚገኘው በመካከለኛው ኡጋንዳ ቡጎሎ ግዛት መሆኑም ተዘግቧል።
ተጠርጣሪዎቹ ከሌላ ግዛት የመጡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም ተብሏል።
የቡጎሎ ግዛት የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሐሰን እንኩንቱ ማክሰኞ እለት እንደተናገሩት ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር የዋሉት የያዙት የመታወቂያ ፎቶ ባለመሳሰሉ ነው ተብሏል።
"ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ፈተናውን ለመቆጣጠር በመጣ አንድ ግለሰብ ነው። የኡጋንዳ ብሔራዊ ፈተና ቦርድ ለተማሪዎቹ ከሰጣቸው የመታወቂያ ፎቶ ጋር ባለመሳሰሉ ተይዘዋል" ብለዋል።
የቀጠናው የፖሊስ አቀባይ ሔለን ቡቶቶ እንዳሉት የትምህርት ቤቱን አስተዳደር ስለ ጉዳዩ እንጠይቃለን ብለዋል።












