ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሞዛምቢክ መንግሥት ለፖፕ ፍራንሲስ ጉብኝት 9.6 ሚሊዮን ብር አወጣለሁ ማለቱ እያወዛገበ ነው
የሞዛምቢክ መንግሥት በሚቀጥለው ሳምንት ይጎበኛሉ ተብለው ለሚጠበቁት ፖፕ ፍራንሲስ 325ሺ ዶላር (9.6 ሚሊዮን) ብር ለማውጣት ማቀዱን የሃገሪቱ ሬዲዮ የዘገበ ሲሆን ይህ ሁኔታ ግን የሞዛምቢክ ዜጎችን አላስደሰተም።
"እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የሚሆን መሰረታዊ በጀት ያለን ሲሆን እሱንም አስተካክለን ለፖፑ ጉብኝት እናውለዋለን" በማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆስ ፓቺዮ ለሞዛምቢክ ሬድዮ ተናግረዋል።
የሞዛምቢኳ መዲና ማፑቶ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የከተማን ሁኔታ ለማሻሻል ጠቃሚ የሚሉት ግለሰብ ጉብኝት መጠበቅ የለበት፤ ገንዘቡ ለከተማዋ መዋል አለበት ብለዋል።
"ይሄ ድድብና ነው! ለምንድንነው ከተማችንን ውብ ለማድረግ የፖፑ ጉብኝት የሚጠበቀው? ማፑቶ ሁልጊዜም ቢሆን እንዲህ ነው መምሰል ያለባት" በማለት ቤርኒሺያ ኮቴላ የተባለች ነዋሪ ተናግራለች
"ሰው ገላውን ሳይታጠብ ቅባት መቀባት እንደማለት ነው። እንዲህ አይነት ምስል መፍጠር ለምን አስፈለገ? ይህ እውነታውን ለመደበቅ የተደረገ ነው" ብላለች
አፎንሶ ሲልቬይራ የተባለ ነዋሪ ለፖፑ ጉብኝት ተብሎ የተያዘው በጀት የፖፑን ደህንነት ለማስጠበቅ ከመዋሉ ጋር ተያይዞ ትክክል ነው ብሎ ያምናል። መንገዶቹ፣ ካቴድራሉና ስታዲየሞቹ ጥብቅ ቁጥጥር ስለሚያስፈልጋቸው
"የከተማ ፅዳት፣ እድሳትና ቁጥጥር የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም መሆን አለበት" ይላል።