በዩኬ የ16 እና 17 ዓመት ታዳጊዎች በምሽት ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሰዓት እላፊ ገደብ ሊጣል ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩናይትድ ኪንግደም ከ16 ዓመት በላይ የሆኑ ታዳጊዎች የማኅበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የምሽት የሰዓት እላፊ የሚጥል ዕቅድ ወጣ።
ታዳጊዎቹ የአካውንታቸውን መለያ በማስተካከል ግን እግዱን ማለፍ ይችላሉ።
የሰዓት እላፊ ደገቡ እንደ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ እና ዩቱዩብ የመሰሉ መተግበሪያዎች ለ16 እና 17 ዓመት ታዳጊዎች ከእኩለ ሌሊት እስከ ንጋት ጠዋት ድረስ እንዳይሠሩ የሚያደርግ ነው።
የአገሪቱ መንግሥት “ሱስ አስያዥ” የሆኑ እንደ ‘አውቶ ፕለይ’ እና ያለማቋረጥ ‘ስክሮል’ ያሉ አሠራሮችን ለማስቆም ፍላጎት አለው።
ይህ እርምጃ ከሰዓት እላፊ ገደቡ ጋር ተጨምሮ የታዳጊዎችን ትኩረት፣ እንቅልፍ እና የቤተሰብ ሕይወት ያሻሽላል ተብሏል።
ይሁን እንጂ የመንግሥት ዕቅድ ታዳጊዎችን ልቅ ከሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የሚገታ አይደለም በሚል ጠንካራ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እየወተወቱ ነው።
አዲሱ ዕቅድ ባለፈው ሰኔ ወር ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ የዩኬ ታዳጊዎች በርካታ መድረኮችን እንዳይጠቀሙ መታገዳቸውን ተከትሎ የተሰማ ነው።
የዩኬ የበይነ መረብ ደኅንነት ሚኒስትር የሆኑት ኬኒሻካ ናራያን ለቢቢሲ ፖሊሲውን ተከላክለው የሞገቱ ሲሆን፤ አሠራሮች ላይ የሚደረጉ ለውጥች እና የሰዓት ገደቡ ብሪታኒያ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ጠበቅ ያሉ እርምጃዎችን የምትወስድ አገር ያደርጋታል ብለዋል።
አዲስ የቀረበው ዕቅድ ከወራት በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቀጣይ እርምጃዎች የታዳጊዎች “የኤአይ ቻትቦት” ደኅንነት ላይ እንደሚወሰዱ አመልክቷል።





















