የኢራን ፓርላማ አባላት ለመሪያቸው ግድያ የሚወሰድን የበቀል እርምጃ እንደሚደግፉ አሳወቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአንድ መቶ ሰማኒያ በላይ የኢራን ፓርላማ አባላት አገራቸው በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት የተገደሉትን ጠቅላይ መሪ ደም ለመበቀል በምታደርገው ሁሉ በአንድነት እንደሚቆሙ ቃል ገቡ።
አባላቱ በጻፉት ደብዳቤ የአገሪቱ ታላላቅ የሃይማኖት እና የመንግሥት አካላት፤ የአገሪቱን መሪ የገደሉትን መበቀላቸው አስገዳጅ ነው የሚል ውሳኔ አስተላልፈዋል። "ለሚወሰደው ተግባራዊ እርምጃ” ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም አሳውቀዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ለወራት የዘለቀውን ጦርነት በኢራን ላይ በከፈቱበት የመጀመሪያ ዕለት እና ከዚያ በኋላ ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና ሌሎች በርካታ የፖለቲካ እንዲሁም ወታደራዊ መሪዎች ተገድለዋል።
ጠቅላይ መሪው ከተገደሉ ከአራት ወራት በኋላ ስንብት እና ቀብር ባለፈው ሳምንት ለቀናት በዘለቀ ከፍተኛ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
የኢራን ባለሥልጣናት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ታድመውበታል ባሉት የስንብት ሥነ ሥርዓቶች ላይ የተገኙ ኢራናውያን ለተፈጸመው ግድያ መንግሥታቸው የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
ለዚህም ዋነኛው ዒላማ ናቸው ያሏቸውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን ስም እና ምሥል ይዘው ነበር።
በተያያዘም ኢራን ፕሬዝዳንት ትራምፕን ለመግደል አዲስ ዕቅድ ስለማውጣቷ እስራኤል አገኘሁት ያለችውን መረጃ ለአሜሪካ መስጠቷን ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ዘግቧል።





















