ቀጥታ, አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ስታስፋፋ፣ ኢራን ምላሿ የበለጠ የከፋ እንደሚሆን አስታወቀች

የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ዛሬ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በኢራን ላይ ከፍተኛ ተከታታይ ጥቃት መፈጸሙን ሲያስታውቅ፣ ኢራን የአጸፋ ምላሿ ዒላማ የሚሆኑ ተቋማትን መጠን እንደምትጨምር ገለጸች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. 300 በላይ ናይጄሪያውያን ከደቡብ አፍሪካ ወደ አገራቸው ተመለሱ

    ናይጄሪያ በቅርብ ወራት በተደረጉ ተቃውሞች ምክንያት ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ለተመለሱ ዜጎቿ ካሳ ልትጠይቅ መሆኑን አስታውቃለች።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ናይጄሪያ በቅርብ ወራት በተደረጉ ተቃውሞች ምክንያት ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ለተመለሱ ዜጎቿ ካሳ ልትጠይቅ መሆኑን አስታውቃለች

    ናይጄሪያ ስድስተኛው እና የመጨረሻ ነው ባለችው ጉዞ ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑ 306 ሰዎችን ወደ አገራቸው መመለሷን አስታወቀች።

    ተመላሾቹ ዛሬ ረፋድ ላይ በሌጎስ በሚገኘው ሙርታላ ሙሐመድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ደርሰዋል።

    በደቡብ አፍሪካ መጤ ጠል ዘመቻ ዳግም ካገረሸ በኋላ ወደ አገራቸው በፈቃደኝነት የተመለሱት ናይጄሪያውያን ቁጥር ከ1200 በላይ መሆኑ ተገልጿል።

    በደቡብ አፍሪካ በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ የተጀመረው መጤ ጠል እንቅስቃሴ በብዛት ሰላማዊ የነበረ ቢሆንም፤ ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ብጥብጥ፣ ማስፈራራት እና የሕይወት መጥፋት ተከስቷል።

    የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በተፈጠሩ ክስተቶች ዙሪያ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

    የናይጄሪያ መንግሥት ንግዳቸውን፣ ቤታቸውን እና ያላቸውን ንብረት ትተው ከደቡብ አፍሪካ እንዲወጡ ለተደረጉ ዜጎቹ ካሳ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።

    የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ምንም ዓይነት ካሳ እንደማይከፍሉ ተናግረዋል።

    በናይጄሪያ ምክር ቤት የዲያስፖራ ጉዳዮች ኮሚቴ በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ስደተኛ ዜጎቹ ላይ የደረሰውን እና ከአገር መውጣታቸውን ተከትሎ የሁለቱ አገራት ግንኙነትን እያጤነው መሆኑን አስታውቋል።

    የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከአምስት ሳምንታት በፊት "የስደተኞች አስተዳደር" ላይ ዘመቻ ከከፈተ በኋላ ከ53,000 በላይ የውጭ ዜጎች ከአገር መባረራቸውን ወይንም እንዲወጡ መደረጋቸውን አስታወቀ።

    እነዚህ ስደተኞች ከማላዊ፣ ከዚምባብዌ እና ከሞዛምቢክ የመጡ መሆናቸውን የገለጹት ባለሥልጣናቱ፤ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

    በደቡብ አፍሪካ ለተከታታይ ሳምንታት ፀረ ስደተኛ ሰልፎች ከተካሄዱ እንዲሁም አለመረጋጋት፣ ማስፈራራት እና ዘረፋ ከተፈጸመ በኋላ በአገሪቱ ያለ ሕጋዊ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ የሚገኙ ስደተኞች ላይ ሰፊ የተባለ ዘመቻ እያካሄደች ትገኛለች።

  2. አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ስታስፋፋ፣ ኢራን ምላሿ የበለጠ የከፋ እንደሚሆን አስታወቀች

    የአሜሪካ የጦር መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ዛሬ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በኢራን ላይ ከፍተኛ ተከታታይ ጥቃት መፈጸሙን ሲያስታውቅ፣ ኢራን የአጸፋ ምላሿ ዒላማ የሚሆኑ ተቋማትን መጠን እንደምትጨምር ገለጸች።

    በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ሰባት ሰዓት ተኩል ላይ አሜሪካ የፈጸመችው ጥቃት ኢራን በሆርሙዝ ወሽወመጥ በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እንዳትፈጽም ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተገልጿል።

    ማዕከላዊ ዕዙ በኤክስ ገጹ ላይ ባሠራጨው መረጃ "እነዚህ ጥቃቶች የኢራን ኃይሎች በሆርሙዝ ወሽመጥ በጭነት መርከቦች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙበትን ወታደራዊ አቅም የበለጠ ለማዳከም” የተፈጸሙ መሆናቸውን አስታውቋል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ አሜሪካ በኢራን ላይ ማካሄድ የቀጠለችው ጥቃት ኢራን በአጸፋ ጥቃት ዒላማ የምታደርጋቸውን ተቋማት እንድታሰፋ ሊያደርጋት እንደሚችል አስጠንቅቋል።

    በዚህም በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ አጋር የሆኑ አገራት የነዳጅ እና የጋዝ ምርቶች ማውጫዎች፣ ማጣሪያዎች እና መተላለፊያዎች ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጿል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ባለፉት ቀናት ተከታታይ ጥቃቶችን እየፈጸመች ሲሆን፣ ኢራንም በምላሹ በዮርዳኖስ፣ በባህሬን፣ በኩዌት እና በአረብ ኤምሬትስ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት እያደረሰች ነው።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ካበቃ በኋላ በቀጠለው ጥቃት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች የጥቃት ዒላማ እየሆኑ ነው።

    አሜሪካ የኢራንን ጥቃት ለመከላከል በሆርሙዝ ላይ ጥበቃ እያካሄደች መሆኗን እና ወደ ኢራን የሚያቀኑ እና ከኢራን የሚነሱ ሁሉም መርከቦች በመተላለፊያው በኩል እንዳያቋርጡ ዕገዳ ጥላለች።

  3. በዩኬ የ16 እና 17 ዓመት ታዳጊዎች በምሽት ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሰዓት እላፊ ገደብ ሊጣል ነው

    ስልካቸውን እየተጠቀሙ ያሉ ታዳጊዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዩናይትድ ኪንግደም ከ16 ዓመት በላይ የሆኑ ታዳጊዎች የማኅበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የምሽት የሰዓት እላፊ የሚጥል ዕቅድ ወጣ።

    ታዳጊዎቹ የአካውንታቸውን መለያ በማስተካከል ግን እግዱን ማለፍ ይችላሉ።

    የሰዓት እላፊ ደገቡ እንደ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ እና ዩቱዩብ የመሰሉ መተግበሪያዎች ለ16 እና 17 ዓመት ታዳጊዎች ከእኩለ ሌሊት እስከ ንጋት ጠዋት ድረስ እንዳይሠሩ የሚያደርግ ነው።

    የአገሪቱ መንግሥት “ሱስ አስያዥ” የሆኑ እንደ ‘አውቶ ፕለይ’ እና ያለማቋረጥ ‘ስክሮል’ ያሉ አሠራሮችን ለማስቆም ፍላጎት አለው።

    ይህ እርምጃ ከሰዓት እላፊ ገደቡ ጋር ተጨምሮ የታዳጊዎችን ትኩረት፣ እንቅልፍ እና የቤተሰብ ሕይወት ያሻሽላል ተብሏል።

    ይሁን እንጂ የመንግሥት ዕቅድ ታዳጊዎችን ልቅ ከሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የሚገታ አይደለም በሚል ጠንካራ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እየወተወቱ ነው።

    አዲሱ ዕቅድ ባለፈው ሰኔ ወር ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ የዩኬ ታዳጊዎች በርካታ መድረኮችን እንዳይጠቀሙ መታገዳቸውን ተከትሎ የተሰማ ነው።

    የዩኬ የበይነ መረብ ደኅንነት ሚኒስትር የሆኑት ኬኒሻካ ናራያን ለቢቢሲ ፖሊሲውን ተከላክለው የሞገቱ ሲሆን፤ አሠራሮች ላይ የሚደረጉ ለውጥች እና የሰዓት ገደቡ ብሪታኒያ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ጠበቅ ያሉ እርምጃዎችን የምትወስድ አገር ያደርጋታል ብለዋል።

    አዲስ የቀረበው ዕቅድ ከወራት በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቀጣይ እርምጃዎች የታዳጊዎች “የኤአይ ቻትቦት” ደኅንነት ላይ እንደሚወሰዱ አመልክቷል።

  4. አሜሪካ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የኢራን ዲጂታል ሃብት ላይ ማዕቀብ ጣለች

    ስኮት ቤሳንት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የኢራን ዲጂታል ሃብት ላይ ማዕቀብ መጣሉን የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት ተናገሩ።

    በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ “የአሜሪካ ግምጃ ቤት የዲጂታል ሃብት ብዝበዛን ጨምሮ የኢራንን ሕገ ወጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ለመግታት ቁርጠኛ ነው” ብለዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት የውጭ ሃብት ቁጥጥር ክፍል ከኢራን ብሔራዊ ባንክ ጋር የተያያዙ በርካታ አካውንቶች ላይ ማዕቀብ እንደጣለ አስታውቀዋል።

    “ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር የማስገባት ሒደትን በማስቆም የኢራን መንግሥት የሚያገኘውን ያልተገባ ገቢ እንገታለን” ሲሉም ተናግረዋል።

    ማዕቀብ የተጣለባቸው የኢራን አካውንቶች ማዕቀብ በተጣለባቸው የቴህራን ባክኮች ስም በየዓመቱ “በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር” ገንዘብ እንደሚያንቀሳቅሱ ተመልክቷል።

    የኢራን መንግሥትን ሕገ ወጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ በወረቀት ላይ ብቻ ያሉ ሐሰተኛ ኩባንያዎች መጠቀማቸውም ተጠቅሷል።

  5. ለኢራን መረጃ አሳልፎ ሰጥቷል የተባለ የእስራኤል ወታደር ተፈረደበት

    የኢራን እና እስራኤል ሰንደቅ ዓላማ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ለኢራን በመሰለል የተከሰሰ አንድ የእስራኤል ጦር ሠራዊት አባል በወታደራዊ ፍርድ ቤት የአምስት ዓመታት እስር እንደተፈረደበት የእስራኤል መካለከያ ኃይል አስታወቀ።

    ወታደሩ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ሲል በጦርነት ወቅት ከኢራን የተተኮሰ ሚሳዔል ሲከሽፍ የሚያሳይ ቪዲዮን ጨምሮ ለኢራን የስለላ ወኪል መረጃዎችን በማስተላለፍ ነው የተከሰሰው።

    የእስራኤል የመከላከያ ኃይል እንዳለው ወታደሩ ምሥጢራዊ የደኅንነት መረጃ ቪዲዮዎች እና ፎቶግራፎችን በመላክ ገንዘብ እንደሚያገኝ የሚገልጹ በርካታ የቴሌግራም መልዕክት ልውውጦችን አድርጓል።

    በዚህም ወታደሩ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ እስራኤል ከኢራን ጋር ባደረገችው የ12 ቀናት ጦርነት ወቅት ሁለት ቪዲዮዎችን እንደላከ እና "ለእነሱም ክፍያ እንደተቀበለ" የእስራኤል ጦር ተናግሯል።

    በጦርነቱ ወቅት በኢራን ጥቃት በተጎዱ ቦታዎች በሚደረግ የቪዲዮ ቀረጻ ላይ ከባድ ገደቦች ተጠጥለው የነበረ ቢሆንም፣ ወታደሩ በከተማ አካባቢዎች የተቀረጹ በርካታ ቪዲዮዎችን ለ"ኢራናዊው ወኪል" አጋርቷል ሲል አክሏል።

  6. ኢራን ወደ ውይይት ካልተመለሰች የኃይል ማመንጫዎቿ እና ድልድዮቿ እንደሚመቱ ትራምፕ አስጠነቀቁ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ኢራን ወደ ውይይት ካልተመለሰች የኃይል ማመንጫዎቿ እና ድልድዮቿ ላይ በቀጣይ ሳምንት ጥቃት እንደሚሰነዘር ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስጠነቀቁ።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲሆን፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች 20% ክፍያ እንዲፈጽሙ ያቀረቡትን ሐሳብም ሰርዘዋል።

    ትራምፕ በኢራን ወደቦች ላይ የጣሉት እገዳ ግን ባለበት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

    “በቀጣይ ሳምንት ነገሮች የከፉ ይሆኑባቸዋል። ወደ ድርድር ጠረጴዛው የማይመለሱ ከሆነ የኃይል ማመንጫዎቻቸውን እናፈርሳለን፤ ድልድዮቻቸውን እናፈርሳለን” ብለዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ባለሥልጣን ቮልከር ቱርክ የትራምፕን ዛቻ ኮንነዋል።

    ትራምፕ በኢራን የሲቪሎች መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ለማድረስ መዛታቸው “በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ” መሆኑን ገልጸዋል።

    “ሆነ ብሎ ንጹኃን ዜጎች ላይ እና መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት መፈጸም የጦር ወንጀል ነው" በማለትም አክለዋል።

  7. የኢራን ፓርላማ አባላት ለመሪያቸው ግድያ የሚወሰድን የበቀል እርምጃ እንደሚደግፉ አሳወቁ

    የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት

    ከአንድ መቶ ሰማኒያ በላይ የኢራን ፓርላማ አባላት አገራቸው በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት የተገደሉትን ጠቅላይ መሪ ደም ለመበቀል በምታደርገው ሁሉ በአንድነት እንደሚቆሙ ቃል ገቡ።

    አባላቱ በጻፉት ደብዳቤ የአገሪቱ ታላላቅ የሃይማኖት እና የመንግሥት አካላት፤ የአገሪቱን መሪ የገደሉትን መበቀላቸው አስገዳጅ ነው የሚል ውሳኔ አስተላልፈዋል። "ለሚወሰደው ተግባራዊ እርምጃ” ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም አሳውቀዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ለወራት የዘለቀውን ጦርነት በኢራን ላይ በከፈቱበት የመጀመሪያ ዕለት እና ከዚያ በኋላ ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና ሌሎች በርካታ የፖለቲካ እንዲሁም ወታደራዊ መሪዎች ተገድለዋል።

    ጠቅላይ መሪው ከተገደሉ ከአራት ወራት በኋላ ስንብት እና ቀብር ባለፈው ሳምንት ለቀናት በዘለቀ ከፍተኛ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

    የኢራን ባለሥልጣናት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ታድመውበታል ባሉት የስንብት ሥነ ሥርዓቶች ላይ የተገኙ ኢራናውያን ለተፈጸመው ግድያ መንግሥታቸው የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

    ለዚህም ዋነኛው ዒላማ ናቸው ያሏቸውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን ስም እና ምሥል ይዘው ነበር።

    በተያያዘም ኢራን ፕሬዝዳንት ትራምፕን ለመግደል አዲስ ዕቅድ ስለማውጣቷ እስራኤል አገኘሁት ያለችውን መረጃ ለአሜሪካ መስጠቷን ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ዘግቧል።

  8. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሆርሙዝ ‘ከኢራን በስተቀር’ ለሁሉም መርከቦች እንቅስቃሴ ክፍት ነው አሉ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወሳኝ የነዳጅ እና የጋዝ መተላለፊያ የሆነው ሆርሙዝ ወሽመጥ ከኢራን መርከቦች በስተቀር በሌሎች አገራት ለሚደረጉ የባሕር ጉዞዎች ክፈት ነው አሉ።

    ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ሆርሙዝ “ከኢራን በስተቀር ለሌሎች ሁሉም የመርከቦች እንቅስቃሴ ክፍት ነው” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ፤ የኢራን መርከቦች በመተላለፊያው እንዳይንቀሳቀሱ ያገዱት “ወደ ሙሉ ውድመት እያመሩ ባሉት ውሸታም፣ ጠበኛ እና አደገኛ መሪዎቿ” ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

    ጨምረውም ለአሁን ዕቀባው “የየትኛውንም ዓይነት የኢራን ጭነቶችን ይዘው ከኢራን እና ወደ ኢራን ወደቦች የሚጓዙ መርከቦችን ብቻ” የሚመለከት መሆኑን፤ ነገር ወደ “ሙሉ ዕቀባ” እንደሚሸጋገር አመልክተዋል።

    ጀልባዎች እና መርከቦች በሆርሙዝ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  9. እስራኤል ለማንኛውም የኢራን ጥቃት የምትሰጠው ምላሽ “እጅግ ኃይለኛ” እንደሚሆን ኔታንያሁ ተናገሩ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ኢራን አስቀድማ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ አገራቸው የምትሰጠው የአጸፋ ምላሽ ከዚህ ቀደሞ ከነበረው “በበለጠ እጅግ ኃይለኛ” እንደሚሆን አስጠነቀቁ።

    “ለኢራን መሪዎች ይህንን እናገራለሁ፤ የምታጠቁን ከሆነ [አሁን] ነገሮች ዝም ማለታቸው ላይ እንዳትተማመኑ” ሲሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ቪዲዮ ተናግረዋል።

    ከዚህ ቀደም ኢራን ጥቃት ስትፈጽም የተወሰደው አጸፋ “ቀድሞውንም ኃይለኛ” የነበረ ቢሆንም በቀጣይ የሚኖረው የእስራኤል ምላሽ ግን ተመሳሳይ እንደማይሆን ገልጸዋል።

    “አንድ አካል ሲያጠቃን በሁለት እጥፍ መልሰን የማናጠቃባቸው ቀናት አልፈዋል” ሲሉም ተደምጠዋል።

    “ይህንን በኢራን የክፋት ጥምረት ላይ አድርገዋል፤ ሊጎዳን በሚፈልግ ማንኛው አካል ላይ ማድረጋችንን እንቀጥላለን። የምናደርገው እንደዚያ ነው” በማለት በቪዲዮ መልዕክታቸው ተናግረዋል።

  10. የአውሮፓ አየር መንገዶች በፋርስ ባሕረ ሰላጤ አገራት የአየር ክልል እንዳይበሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

    አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአውሮፓ ኅብረት የአየር ትራንስፖርት ደኅንነት ተቋም አየር መንገዶች ጦርነት ባገረሸበት የፋርስ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ ባሉ አገራት እና የባሕር ክልሎች ላይ እንዳይበሩ አስጠነቀቀ።

    ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አሜሪካ እና ኢራን እያካሄዱት ባለው ጥቃት ሳቢያ ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ከተባባሰ በኋላ ወሳኙ የባሕር ላይ መተላለፊ ሆርሙዝ ተዘግቷል።

    አሁን ደግሞ የአውሮፓ የአየር ትራንስፖርት ደኅንነት ተቋም የመጓጓዣ አውሮፕላኖች በባህሬን፣ በኩዌት፣ በኳታር፣ በአረብ ኤምሬት እንዲሁም በባሕረ ሰላጤ ላይ እንዳይበሩ አስጠንቅቀወል።

    ተቋሙ እንዳለው "ተገማች ያልሆኑ ወታደራዊ ሁኔታዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ሚሳዔሎች፣ ድሮኖች፣ ተዋጊ አውሮፕላኖች እና የአየር መከላከያ ሥርዓቶች በአንድ ላይ” በቀጣናው በሚደረጉ የአየር ትራንስፖርት በረራዎች ላይ “ከፍተኛ አደጋን” ደቅነዋል።

    ተቋሙ ለአየር መንገዶች የሰጠው ማስጠንቀቂያ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ መሆኑን እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ አካበቢ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እንደሚከታተል ገልጿል።

  11. በኦማን ባሕር ዳርቻ መርከብ ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ በኢራን ከተሞች ፍንዳታ ተሰማ

    በባንዳር አባስ የተፈጸመው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, US Central Command

    የምስሉ መግለጫ, በባንዳር አባስ የተፈጸመው ጥቃት

    የኢራን የሲቪል ኒውክሌር ጣቢያ በሚገኝበት ቡሼህር ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ፍንዳታዎች መሰማታቸውን የቴህራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ሌላኛው የወደብ ከተማ ባንዳር አባስ እና አባዳን ከተማም እንደተመቱ ተገልጿል። የኢራን መገናኝ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያሳየው ብቸኛው የኢራን የሲቪል ኒውክሌር ጣቢያ በሚገኝባት ቡሼህር ከተማ ውስጥ በአራት የተለያዩ ቦታዎች ጥቃት ተፈጽሟል።

    የግዛቱ ምክትል ገዥ ኢህሳን ጃሃኒአን በከተማው የሚገኙ “የተለያዩ አካባቢዎች በጠላት ተተኳሾች” ተመትተዋል ማለታቸውን መንግሥታዊው የዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል። ወደብ ከተማ በሆነው ማህሻህርም ፍንዳታ መሰማቱን መገናኝ ብዙኃኑ አስታውቀዋል።

    እነዚህ ጥቃቶች መፈጸማቸው የተሰማው፤ በኦማን ባሕር ዳርቻ ላይ አንድ ነዳጅ ጫኝ መርከብ “ባልታወቀ የውጭ መሣሪያ” እንደተመታ ከተገለጸ በኋላ ነው።

    የመርከቡ ባለቤት የሆነው ኩባንያ እንደገለጸው ‘ስቶልት ማግኒዚየም’ የተባለው ነዳጅ ጫን የተመታው በአረቢያን ባሕር ላይ እየተጓዘ በነበረበት ሰዓት ነው። የመርከቡ የሞተር ክፍል እሳት ቢያያዝም የተጎዳ ሰው አለመኖሩ ተገልጿል።

    በተጨማሪም ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲገወዙ የነበሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መምታቷን አስታውቃለች።

    በዚህ ጥቃት ሕንዳዊ ባሕርተኛ መገደሉን ያስታወቀው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መከላከያ ሚኒስቴር እርምጃ “ድፍረት የተሞላበት” እርምጃ አውግዟል።

  12. ሕንድ በተገደለባት ባህረተኛ ጉዳይ ለመነጋገር የኢራንን አምባሳደር ጠራች

    የሕንድ የውጭ ጉዳዮች ሚኒስቴር  ቃል አቀባይ ራንድሂር ጃይስዋል

    የፎቶው ባለመብት, Hindustan Times via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የሕንድ የውጭ ጉዳዮች ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ራንድሂር ጃይስዋል

    የሕንድ የውጪ ጉዳዮች ሚኒስቴር ኢራን በሆርሙዝ ወሸመጥ ሁለት መርከቦች ላይ በፈጸመችው ጥቃት አንድ ባህረተኛ ሲገደል 10 ደግሞ መቁሰላቸውን አስታወቀች።

    “አል ባሂያህ እና ሞምባሳ” የተባሉት ሁለት መርከቦች በኦማን የባህር ዳርቻ ባሉበት በኢራን የክሩዝ ሚሳዔል ጥቃት ሲደርስባቸው 46 ሠራተኞችን ይዘው እንደነበር ተገልጿል።

    በአል ባሂያህ መርከብ ላይ ከነበሩት 12 ሕንዳውያን መካከል አንዱ ሲገደል ሌላው ደግሞ ጉዳት ደርሶበታል ሲሉ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ራንድሂር ጃይስዋል በኤክስ ጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ሞምባሳ በተሰኘችው መርከብ ላይ 18 ሕንዳውያን የነበሩ ሲሆን ዘጠኙ በጥቃቱ ቆስለዋል። ከቆሰሉት መካከል ሁለቱ የጉዳታቸው መጠን ከፍተኛ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

    የሕንድ የውጭ ጉዳዮች ሚኒስቴር የኢራን ምክትል አምባሳደርን ጠርቶ “በጥቃቱ ላይ ያለውን ጠንካራ ተቃውሞ” እንደሚገልጽ አስታውቋል።

    “እነዚህን ጥቃቶች እና ባህረተኞችን ዒላማ የሚያደርግ ግጭትን፣ እንዲሁም እንደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ያለ ዓለም አቀፍ ውሃ ላይ የሚደረግ ነጻ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴን ማደናቀፍ አጥብቀን እናወግዛለን።”

  13. ዩኬ ሚስቱን እና ሁለት ልጆቹን በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብ ተላልፎ እንዲሰጣት ጠየቀች

    የ45 ዓመቱ ተጠርጣሪ ዶዳና ሚሃንይሲ ቲሹማ
    የምስሉ መግለጫ, የ45 ዓመቱ ተጠርጣሪ ዶዳና ሚሃንይሲ ቲሹማ አርብ ዕለት በጆሃንስበርግ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቧል

    ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቤድፎርድሻየር ሚስቱን እና ሁለት ሴት ልጆቹን በመግደል የተጠረጠረውን ግለሰብ ደቡብ አፍሪካ አሳልፋ እንድትሰጣት ጠየቀች።

    ተጠርጣሪው ዩኬ ተላልፎ እንዲሰጣት ጥያቄ ካቀረበች በኋላ በደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

    ኔታቦ ዛንዲል ቲሹማ የተባለችው የ42 ዓመት ሴት እና ናታሌ እና ናላ የተባሉት የ15 ዓመት እና የአምስት ዓመት ሴት ልጆቿ በቤድፎርድ አቅራቢያ ግሬት ዲንሃም በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሕይወታቸው አልፎ በፖሊስ የተገኙት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

    እናት እና ልጆቹ በደረሰባቸው አካላዊ ጉዳት መሞታቸው በአስክሬን ምርመራ ተረጋግጧል።

    አቃቤ ሕግ በ45 ዓመቱ ዶዳና ሚሃንይሲ ቲሹማ ላይ ሦስት የግድያ ክሶችን አቅርቧል።

    በጆሃንስበርግ በሚገኘው ማጂስትሬት ፍር ድቤትም ቀርቧል። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመመልከት ለሐምሌ 22 ተጨማሪ ቀጠሮ ሰጥቷል።

    ግለሰቡ ለንደን ከሚገኘው ሂትሮ አየር ማረፊያ ተነስቶ በዱባይ በኩል ደቡብ አፍሪካ መግባቱም ተገልጿል።

    ከዚያም ወደ ጆሃንስበርግ ከመመለሱ በፊት ወደ ዚምባብዌ መሄዱን ፖሊስ አስታውቋል።

    አርብ ዕለትም በኬንሲንግተን ከተማ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

    የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ቀል አቀባይ አትሌንዳ ማቴ፣ ከማንችስተር ኢንተርፖል ለፕሪቶሪያ ኢንተርፖል ጥያቄው መቅረቡን አረጋግጠው፣ ሰነዶችን እና ማስረጃዎችን ጨምሮ የተሟላ ጥያቄ በ40 ቀናት ውስጥ እንዲቀርብላቸው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

    የ42 ዓመቷ ኔታቦ ዛንዲሌ ከ15 ዓመት እና ከአምስት ዓመት ሴት ልጆቿ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Bedfordshire Police

    የምስሉ መግለጫ, የ42 ዓመቷ ኔታቦ ዛንዲሌ እና የ15 ዓመት እና የአምስት ዓመት ሴት ልጆቿ ቤታቸው ውስጥ ሞተው የተገኙት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ነበር
  14. በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለው ግጭት በመባባሱ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ

    የነዳጅ መቅጃ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ያገረሸው ጦርነት በመባባሱ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ።

    በእስያ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን አንድ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ1.9 በመቶ አሻቅቦ በበርሜል 84.87 ዶላር ደርሷል።

    በአሜሪካ ገበያ ደግሞ በ2 በመቶ ጨምሮ በበርሜል 79.75 ዶላር እየተሸጠ ነው።

    ግጭቱ ተባብሶ በመቀጠሉ ሰኞ ዕለት የብሬንት ነዳጅ ዋጋ በ3 በመቶ ገደማ የጨመረ ሲሆን በአራት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

    ከግጭቱ ጋር ተያይዞ ነጋዴዎች በሚሰጡት ምላሽ ዓለም አቀፍ የጅምላ ገበያ ዋጋ ከቅርብ ወራት ወዲህ እየዋዠቀ ነው።

    አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት መጨረሻ በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለች።

    ወሽመጡ 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ ዘይት እና የተጣራ የተፈጥሮ ጋዝ የሚተላለፍበት ዋነኛ መስመር ነው።

    አሁን ላይ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ቢታይም ሚያዝያ ወር ላይ ከነበረው እጅግ ያነሰ ነው።

    ሚያዚያ ወር ላይ የአንድ በርሜል ብሬንት ዋጋ 120 ዶላር ደርሶ ነበር።

  15. ኢራን በባሕሬን እና በዮርዳኖስ በሚገኙ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ፈፀመች

    ነዳሥ ጫን መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በባሕረ ሰላጤው የሚገኙት ዮርዳኖስ እና ባሕሬን በግዛታቸው ውስጥ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ገለጹ።

    ኢራን ጥቃቱ የፈፀመችው የአሜሪካ ጥቃት ለሦስተኛ ቀን ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው።

    የባሕሬን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሌሊቱን በተለያየ ሰዓት ሦስት ማስጠንቀቂያዎችን በማሰማት ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ወደሚገኝ መጠለያ እንዲገቡ አስጠንቅቋል።

    የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ዘብም በአገሪቷ አሜሪካ የምትገለገልበትን የተለያዩ ሥፍራዎች ዒላማ ማድረጉን ገልጿል።

    አብዮታዊ ዘቡ በኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን - ኢርና - በተጋራ መግለጫው፣ በጥቃቱ በርካታ የጦር መሣሪያ መከማቻዎችን፣ የአሜሪካ ኃይሎች እና የአሜሪካ የባሕር እና አየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ራዳር የሚገኝበትን የሳተላይት ኮሚዩኒኬሽን ማዕከል ማውደሙን አስታውቋል።

    የዮርዳኖስ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባም ዮርዳኖስ ማክሰኞ ጠዋት ላይ በግዛቷ አራት ሚሳኤሎችን እንዳከሸፈች እና በጥቃቱ የደረሰ ሞትም ሆነ የንብረት ውድመት እንደሌለ ገልጿል።

    አብዮታዊ ዘቡ በመግለጫው፣ በዮርዳኖስ የሚገኙ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ማድረጉን ገልጾ፣ ለዮርዳኖስ መንግሥት ወይም ሕዝብ "ጥላቻ" እንደሌለው ገልጿል።

    ከሦስት ቀናት በፊት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለቱ አገራት የደረሱበት የተኩስ አቁም "አብቅቷል" ካሉ በኋላ ያገረሸው ጦርነት፣ የሰላም ተስፋን አመንምኗል።

  16. የአውሮፓ ኅብረት የሱዳን የወርቅ ንግድ ላይ እገዳ ጣለ

    የወርቅ ጥፍጥፍ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ሰኞ ዕለት የሱዳንን የእርስ በእርስ ጦርነት በገንዘብ እየደገፈ ነው ያለውን የአገሪቱ የወርቅ ንግድ ላይ አዲስ እገዳ ጣለ።

    እገዳው “መግዛት፣ ማስመጣት፣ ወይም ከሱዳን የሚገኝ ወርቅን ማዘዋወር” እንደሚያካትት ተገልጿል።

    የአውሮፓ ኅብረት በተጨማሪም የወርቅ ማዕድንን ለማውጣት የሚያገለግሉ “ወደ ሱዳን ሜርኩሪ እና ሲያናይድ መሸጥ፣ ማቅረብ፣ ማዘዋወር ወይም ማስገባት” መታገዱን አስታውቋል።

    የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) የሱዳን የተወሰኑ የወርቅ ማውጫዎችን እንደሚቆጣጠር እና ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ (ዩኤኢ) እንደሚልክ ይነገራል።

    የሱዳን ጦር ኃይሎች (ኤስኤኤፍ) ዩኤኢን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በመደገፍ፣ በሱዳን ውስጥ የድሮን ጥቃቶችን በመፈጸም ይከስሳታል።

    ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ግን ውንጀላውን ታስተባብላለች።

    ሱዳን በአፍሪካ ወርቅ ላኪ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ናት።

  17. ትራምፕ የኢራን ጦርነት መቀጠሉን ለኮንግረስ አሳወቁ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የገቡት ጦርነት ከሰኔ 30 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ዳግም መቀጠሉን ለኮንግረስ በደብዳቤ ማሳወቃቸው ተገለጸ።

    በዚህ ደብዳቤ መሠረት ኮንግረሱ በኢራን ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ይሁንታውን እስኪሰጣቸው ድረስ የ60 ቀናት እድሜ ይኖራቸዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ምንም እንኳ አዳዲስ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ቢቀጥሉም እንዲሁም በወደቦቿ ላይ ዳግም እገዳ ቢጥሉም አሁንም ከቴህራን ጋር የገቡት የተኩስ አቁም ጦርነቱን የማስቆም ዕድል እንዳለው ገልጸዋል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ በዮርዳኖስ፣ ባህሬን እና ኩዌት የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ዒላማዎችን ማጥቃቱን አስታውቋል።

    እሁድ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ ዳግም ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ የአሜሪካ ጦር በኢራን ላይ አዲስ ዙር ጥቃት መክፈቱን አስታውቋል።

    ፕሬዚዳንቱ በደብዳቤያቸው ላይ “አሜሪካውያንን እና የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ፖሊሲ ፍላጎቶችን ለመጠበቅ ባለብኝ ኃላፊነት የተነሳ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ አዝዣለሁ” ብለዋል።

  18. ትራምፕ የሳዑዲው ልዑል በሁቲዎች ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ይሁንታቸውን ሰጡ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ተጨባብጠው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን በሁቲ ታጣቂዎች ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ይሁንታቸውን መስጠታቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ አክሲዮስ ዘገበ።

    ሳዑዲ ሰኞ ዕለት በሰነዓ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን ይህንን ተከትሎ በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች እአአ ከ2022 ወዲህ ትልቅ ነው የተባለ የአጸፋ እርምጃ ወስደዋል።

    ይህም ለአራት ዓመታት ዘልቆ የቆየውን ይፋዊ ያልሆነ የሰላም ስምምነት ያፈረሰ መሆኑ ተገልጿል።

    የሳዑዲው ልዑል አስቀድመው ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት አገራቸው ከሁቲ ታጣቂዎች ጋር ባለው መጠነ ሰፊ ግጭት ዙሪያ ስጋት እንደገባት እና የአሜሪካን ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንደምትፈልግ መጠየቃቸው ተገልጿል።

    ሳዑዲ አረቢያ ይህንን ጠየቀችው ባለፈው ሳምንት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሐሙስ ዕለት በዋሺንግተን የሳዑዲ አምባሳደር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ጋር ተገናኝተዋል።

    ከአንድ ቀን በኋላም ሩቢዮ የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሳል ቢን ፋርሃንን ጋር ተነጋግረዋል።

    አርብ ዕለት ደግሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሳዑዲው ልዑል ጋር በስልክ ተወያይተዋል ተብሏል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት የሳዑዲው ልዑል በሁቲ ላይ የሚፈጸም ወታደራዊ እርምጃን አሜሪካ እንድትደግፍ ትራምፕን መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

    ዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ቢጠየቅም በቀጥታ ምላሽ አልሰጠም።

    በዋሺንግተን የሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲም በዘገባው ላይ ያለው ነገር የለም።

    በሳዑዲ እና በሁቲ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ የተጀመረው ከአስር ቀን በፊት የኢራን አውሮፕላን ሁቲዎች በሚቆጣጠሩት ሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ ካረፈ በኋላ ነው።

    አውሮፕላኑ የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነስርዓትን ላይ ለመገኘት የሚሄዱ የልዑካን ቡድንን ጭኖ መመለሱ ተገልጿል።

    ሳዑዲ አረቢያ ከአስር ዓመት በፊት ከኢራን ወደ ሰነዓ የሚደረግ በረራን አግዳለች።

    ሰኞ ዕለት የኢራን አውሮፕላን የልዑካን ቡድንኑን ይዞ ሲመለስ ሳዑዲ የሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያን ደብድባለች።

    አውሮፕላኑ አቅጣጫውን ቀይሮ በአል ሁዳይዳህ ለማረፍ ተገድዷል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ የጦር መሣሪያዎችን፣ የሚሳዔል ክፍሎችን እና ወታደራዊ ባለሙያዎችን ጭኗል ሲሉ ከስሰዋል።

    ሁቲዎች የሳዑዲ ጥቃትን ተከትሎ በደቡብ ምዕራብ ሳዑዲ ወደሚገኘው አብሃ አውሮፕላን ማረፊያ ባሌስቲክ ሚሳዔል አስወንጭፈዋል።

  19. አሜሪካ አዲስ ጥቃት ስትከፍት፤ ኤምሬትስ ኢራን በመርከቦቿ ላይ የፈፀመችውን ጥቃት አወገዘች

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያሉ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኢራን ሰኞ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሁለት የነዳጅ ጫኝ መርከቦቼ ላይ ከባድ ጥቃት ፈፅማለች ስትል ኢራንን ከሰሰች።

    " አሳፋሪ" ስትል በገለፀችው በዚህ ጥቃት አንድ ሰው የተገደለ ሲሆን ስምንት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ገልጻለች።

    ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዋነኛ መተላለፊያ የመዝጋት እቅዷ አካል አድርገው ሁሉም የንግድ መርከቦች 20% ክፍያ እንዲፈጽሙ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል።

    ይህም ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፍ እንዲቻል የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን እንደሚውል አክለዋል።

    የአሜሪካ ጥቃቶች ለሦስተኛ ቀን የቀጠሉ ሲሆን ፕሬዚደንት ትራምፕ ኢራን ‘በከባዱ’ እንደተመታች ተናግረዋል።

    የሁለቱ አገራት ጥቃት ተባብሶ ቀጥሏል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትራምፕ መተለላፊያው ላይ እገዳ መጣላቸውን ተከትሎ ቴህራን የወሽመጡ “ጠባቂ” ሆና ትቀጥለላች ሲሉ ትራምፕ የተጠቀሙትን ቃል በመጠቀም ምላሽ ሰጥተዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመቆጣጠር ያለው ውዝግብ የሁለቱን አገራት ጦርነት ለማስቆም ያለውን ጥረት አመንምኖታል።

    ሆኖም ትራምፕ አሁንም ቢሆን ስምምነት ማድረግ የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል።

    ውጥረቱ በቀጠለበት በዚህ ወቅትም ነው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢራን ክሩዝ ሚሳኤሎች ሁለት የአገሪቷን ታንከሮች ዒላማ ማድረጋቸውን የገለፀችው።

    በጥቃቱ አንድ ሕንዳዊ የመርከበኞች ቡድን አባል ሲገደል፣ ስምንት መቁሰላቸውን እና የአራቱ ከባድ ጉዳት መሆኑን ጠቅሳለች።

    ከተጎዱት መካከል ስድስቱ ሕንዳውያን ሲሆኑ ሁለቱ ዩክሬናዊያን እንደሆኑ የኤምሬስትስ መከላከያ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    “ሚኒስቴሩ ይህንን ዓለም አቀፍ ሕጎች እና ስምምነቶችን በግልጽ የጣሰውን እና በቀጣናው መረጋጋት እና ፀጥታ ላይ ስጋት የደቀነ ጥቃት ያወግዛል” ብሏል።

  20. ትራምፕ በኢራን ወደቦች ላይ በድጋሚ እገዳ ጣሉ

    ሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ በድጋሚ በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ እንደምትጥል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

    በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገጻቸው “የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት ነው፤ ኢራን አለችም አላለችም ተከፍቶ ይቆያል። ኢራን ላይ በድጋሚ እገዳ ይጣላል” ብለዋል።

    እገዳው የኢራን መርከቦች “እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ” እንደሚያደርግ እና ለሌሎች አገራት ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ “ፍትሐዊ እና ክፍት” ሆኖ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

    “ከዚህ በኋላ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥ ጠባቂ ናት” ያሉት ትራምፕ፤ ሁሉም የንግድ መርከቦች 20% ክፍያ እንዲፈጽሙ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል።

    ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፍ እንዲቻል የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን እንደሚውል አክለዋል።

    ትራምፕ ከዚህ ቀደምም በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ ጥለው እንደነበር ይታወሳል።

    ኢራን ከነዳጅ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለመገደብ በሚል የወደብ እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ ተጥሎ ቆይቷል።

    የተባበሩት መንግሥታት የማሪታይም ተቋም እንደሚለው የትኛውም አገር ዓለም አቀፍ መተላለፊያን የመቆጣጠር ሕጋዊ መብት የለውም።

    ኢራን እና አሜሪካ የመግባቢያ ሰነድ ሲፈራረሙ እገዳው ተነስቶ ነበር።

    አሁን ትራምፕ በድጋሚ እገዳውን ጥለው 20% ክፍያ እንደሚኖርም ተናግረዋል።