ቀጥታ, እስራኤልን በመሰለል ለኢራን መረጃዎችን አስተላልፏል የተባለው አሜሪካዊው ተያዘ

አንድ ነዋሪነቱ እስራኤል ውስጥ የሆነ አሜሪካዊ አይሁድ ለኢራን በመሰለል ክስ እንደተመሠረተበት የእስራኤል ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. እስራኤል የኢራን ተደራዳሪዎችን ለመግደል እያሴረች እንደነበር ተዘገበ

    አሜሪካና ኢራን ወሳኝ የሆነውን የተኩስ አቁም ስምምነት በደረሱበት እስራኤል የኢራንን ከፍተኛ ተደራዳሪዎች ለመግደል እያሴረች እንደነበር የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚያምኑ ‘ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ’ ጋዜጣ ዘገበ።

    ባለፈው ሚያዝያ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን በተኩስ አቁም ጋብ ለማድረግ ያስቻለው ንግግር ወደ መቋጫው ሲቃረብ ዋነኛ የኢራን ተደራዳሪዎች የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እና የፓርላማው አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ የእስራኤል ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት አሜሪካ ተፈጥሮባት እንደነበር ባለሥልጣናት መናገራቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።

    እንደ ዘገባው ከሆነ ከፍተኛ ስጋት የተፈጠረበት የትራምፕ አስተዳደር እስራኤል ሁለቱን የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዒላማ ልታደርግ እንደምትችል ቴህራንን እንዲያስጠነቅቁ በአካባቢው አገራት በኩል መልዕክት አስተላልፏል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት በሚያዝያ ወር ድርድሩ ከተጀመረ በኋላ የሚደረግ ማንኛውም የግድያ ሙከራ ውይይቱን እንደሚያቆመው እና ግጭቱን እንደገና እንደሚያባብሰው ስላመኑ ነበር ስጋት የተፈጠረባቸው ተብሏል።

    የኢራኑ ፓርላማ አፈ ጉባዔ እና ዋነኛው ተደራዳሪ ጋሊባፍ የእስራኤል የግድያ ዒላማ ዝርዝር ውስጥ መግባታቸውን አሜሪካ ከተረዳች በኋላ እስራኤል ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳትወስድ እንዳሳሰበች ጋዜጣው ዘግቧል።

    የኢራን ባለሥልጣናት እስራኤል በዲፕሎማሲያዊ ስብሰባዎች ወቅት የድርድር ቡድኗን ዒላማ እንዳታደርግ በፓኪስታን እና በኳታር አሸማጋዮች በኩል የአሜሪካን ዋስትና እንደምትፈልግ መጠየቋንም ጠቅሷል።

    ዘገባው ጨምሮም ሚያዝያ ወር ላይ የኢራን የደኅንነት ኃይሎች ሁለት የእስራኤል አውሮፕላኖች ወደ ኢራን የአየር ክልል መግባታቸውን በመጥቀስ ከፓኪስታን ወደ ቴህራን የመልስ በረራ ወደ ላይ የነበሩት ጋሊባፍ አቅጣጫቸውን ቀይረው ማሽሃድ ወደተባለችው የኢራን ከተማ ማምራታቸውን ገልጿል።

    ዘገባውን በተመለከተ በአሜሪካ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ባለሥልጣናት አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጋዜጣው አመልክቷል።

  2. አሜሪካዊው እስራኤል ውስጥ ለኢራን በመሰለል ተያዘ

    አንድ ነዋሪነቱ እስራኤል ውስጥ የሆነ አሜሪካዊ አይሁድ ለኢራን በመሰለል ክስ እንደተመሠረተበት የእስራኤል ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

    ኢየሩሳሌም ውስጥ ተማሪ የሆነው የ21 ዓመቱ አሜሪካዊ ኤሊ ላቮን በእስራኤል ላይ ለሚያካሂደው ስለላ ከኢራን በኩል በክሪፕቶከረንሲ ክፍያ እንደሚሰጠው ተገልጿል።

    የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ግለሰቡ ከኢራን የስለላ ወኪሎች ጋር ግንኙነት የጀመረው በኅዳር 2025 ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ወደ አሜሪካ በሄደበት ጊዜ በቴሌግራም ላይ ለወጣ የሥራ ማስታወቂያ ምላሽ ከሰጠ በኋላ ነው።

    ከአንድ ወር በኋላም ወጣቱ ወደ እስራኤል ሲመለስ የኢራን የስለላ ተቋምን የወከለ ሰው በቴሌግራም መልዕክት በማስተላለፍ ፎቶዎችን እንዲያነሳ እና ቪዲዮዎችን እንዲቀርጽለት ትዕዛዝ እንደተሰጠው በቀረበበት ክስ ላይ ተመልክቷል።

    በተጨማሪም የተለያዩ ቦታዎችን ቪዲዮ መቅረጹን እና የታዘዘውን መፈጸሙን የሚገልጽ መልዕክት ማስተላለፉ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህ ሥራውም በመቶዎች የሚቆጠር ዶላር በክሪፕቶከረንሲ እንደተከፈለው ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

    እስራኤል ባለፉት ዓመታት በርካታ የስለላ ድርጊቶች ያጋጠሟት ሲሆን አሁን የተከሰሰው ወጣት በዚህ ድርጊት የተያዘ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ነው።

    ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው በኢራን የተመለመሉ ሰላዮች ካስተላለፏቸው ቪዲዮች መካከል በርካታዎቹ ኢራን ላይ በፈጸመቻቸው የሚሳዔል ጥቃቶች ዒላማ ሆነዋል።

    ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በቁጥጥር ስር የዋለው ላቮን ላይ ከውጭ የስለላ ወኪል ጋር በመገናኘት ሁለት ክሶች እንዲሁም ለጠላት ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን አሳልፎ በመስጠት 14 ክሶች እንደቀረቡበት ተዘግቧል።

  3. በፈረንሳይ ከከፍተኛ ሙቀት ጋር በተያያዘ ከ2 ሺህ በላይ ተጨማሪ ሞቶች ተመዘገቡ

    ፈረንሳይ ባለፈው ሳምንት ከ2 ሺህ በላይ ተጨማሪ ሞቶችን መመዝገቧን አስታወቀች።

    ይህ የተመዘገበው በአውሮፓ ከፍተኛው ሙቀት በተመዘገበበት የአውሮፓውያኑ ሰኔ ወር የመጨረሻ ሳምንት ነው።

    በዚህ ሳምንት ከከፍተኛ ሙቀት ጋር ተያይዞ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ቀድሞ ከነበረው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር 29 በመቶ ጨምሯል።

    በፓሪስ ብቻ የሟቾች ቁጥር 62 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል።

    የፈረንሳይ የጤና ሚኒስትር ስቴፋኒ ሪስት ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ሞት መጨመሩን ገልጸዋል።

    በፈረንሳይ ሰኔ 24 በአማካይ ሞቃታማው ቀን ሆኖ አልፏል።

    የሙቀት መጠኑ በመዲናዋ ፓሪስ 41 ዲግሪ ሴትንቲ ግሬድ የነበረ ሲሆን ግማሹ የአገሪቷ ክፍል በቀይ የማስጠንቀቂያ ዞን ውስጥ ገብቷል።

    ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በሌሎች የአውሮፓ ክፍሎችም ሙቀቱ ያየለ ሲሆን አዲስ ሞቶች ተመዝግበዋል።

    የአየር ንብረት ትንበያ ባለሙያዎችም በሚቀጥሉት ቀናት በአሕጉሪቱ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እንደሚኖር አስጠንቅቀዋል።

  4. ዩናይትድ ኪንግደም በየቀኑ ለ30 ደቂቃ በእግር የሚጓዙ ዜጎቿን ልትሸልም ነው

    የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ብሔራዊ ጤና አገልግሎት (NHS) የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ የአገሪቱ ዜጎች ሽልማት መስጠት ሊጀመር ነው።

    አገልግሎቱ ከቀጣዩ የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት አንስቶ ሰዎች በቀን ለ30 ደቂቃ በእግራቸው እንዲጓዙ የሚጠይቀውን ‘ማራቶን ኤ መንዝ’ የተሰኘ መርሃ ግብር ይፋ ያደርጋል።

    መርሃ ግብሩ ይህንን ስያሜ ያገኘው፤ ያለ ማቋረጥ በየቀኑ ለ30 ደቂቃ የሚጓዙ ሰዎች በአንድ ወር ውስጥ የማራቶን ሩጫ ውድድር ርቀት የሆነውን 41 ኪሎ ሜትር መራመድ ስለሚችሉ ነው።

    ተጠቃሚዎች ሞባይል ስልካቸውን ወይም ‘ስማርት ዎች’ በመጠቀም በየቀኑ የተጓዙት ርቀት መጠን ማስመዝገብ ይችላሉ።

    በአንድ ወር ውስጥ የማራቶን ርቀትን መጓዝ የቻሉ ሰዎች ለሽልማት ብቁ እንደሚሆኑ ተገልጿል። ሽልማቱ ጥቅማ ጥቅም እና የዋጋ ቅናሽ ሊሆን ይችላል።

    የዩኬ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት ይህንን መርሃ ግብር ያዘጋጀው፤ኦሊምፒክ ሜዳሊያ አሸናፊው ብሬንዳን ፎስተር ጋር በመተባበር ነው። በየቀኑ የተጓዙት የእርምጃ ብዛት የሚያስመዘግቡ ሰዎችን ብዛት 100,000 እንዲደርስ ለማድረግ ታቅዷል።

    ለመርሃ ግብሩ የሚሆነው የመጀመሪያው በጀት በአገልግሎቱ የሚሸፈን ሲሆን፣ ወደፊት ግን ግዙፍ ኩባንያዎች የሚደግፉት የበጎ አድራጎት እንዲሆን ታስቧል።

    ቢቢሲ ያነጋገራቸው ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች በሃሳቡ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ላውረን አንድሪው የተባለች አንዲት ወጣት ሀሳቡ ጥሩ ነው ብላ እንደምታስብ ተናግራለች።

    “አደርገዋለሁ” የምትለው ላውረን፤ ለሽልማት የተዘጋጀው ጥቅማጥቅም እና የዋጋ ቅናሽ ግን በሌላ ቢቀየር ትመርጣለች። “እርምጃዬ ወደ እንደ መጠጥ እና ምግብ ባሉ በነጻ የሚሰጡ ነገሮች ቢቀየር ለመራመድ ይረዳኛል” ብላለች።

  5. በሶሪያ ዋና ከተማ ካፌ ውስጥ በደረሰ ፍንዳታ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    በማዕከላዊ ደማስቆ በደንበኞች በተሞላ ካፌ ውስጥ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የሶሪያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    የሶሪያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር፤ ካፌ ውስጥ ፈንጂ መሣሪያ ተጠምዶ እንደነበር ገልጿል። ጥቃት የደረሰበት ካፌ ዋና ዋና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከሚገኙበት ‘ፓላስ ኦፍ ጀስቲስ’ ከተባለው ሕንጻ 100 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

    እስካሁን ድረስ ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም። ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተፈጸመ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት 25 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ መሰል ፍንዳታ ሲደርስ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው።

    በወቅቱ ‘ሳራያ አንሳር አል ሱናህ’ የተባለው ጂሃዳዊ ቡድን ከፍንዳታው ጀርባ እጁ እንዳለ ቢገልጽም፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) የተባለውን ቡድን ነበር።

    የአሁኑ ጥቃት ከደረሰበት ካፌ አጠገብ የሚገኝ መደበር ባለቤት የሆነ ግለሰብ ፍንዳታው በሶሪያ የእርስ በእስር ጦርነት ወቅት ደማስቆ ውስጥ ይደርሱ ከነበሩ ፍንዳታዎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነበት ተናግሯል።

    ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጣ አንድ ምስል ላይ እንቅስቃሴ የሌላቸው ቢያንስ ሁለት ሰዎች በካፌው በረንዳ ላይ ተኝተው ያሳያል።

    ከጥቃቱ በኋላ በስፍራው የተገኙት የደማስቆ ገዥ ማህር ማርዋን ኢድሊቢ፤ ለዚህ ገዳይ ጥቃት ተጠያቂ የሆኑ አካላት እንደሚቀጡ ተናግረዋል። “አገሪቱ የመረጋጋት ጊዜ ውስጥ በገባች ቁጥር ተንኮለኛ አካላት ለመበጥበጥ ይሞክራሉ” ሲሉም ወቅሰዋል።

    በእስላማዊ ኃይሎች የሚመሩ አማጺያን ከ13 ዓመት አውዳሚ የእስር በእስር ጦርነት በኋላ ባለፈው ዓመት ታህሳስ ላይ በሽር አል አሳድን ከጣሉ ወዲህ ደማስቆ ውስጥ በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

    ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቱ አህመድ አል ሻራ ወደ ሥልጣን ከወጡ ወዲህ በመላው አገሪቱ ያላቸውን ቁጥጥር ለማጠናከር እና የአገሪቱን ደኅንነት ለመመስ እየታገሉ ነው።

  6. በአፍሪካ እና አውሮፓ የአሜሪካ ምድር ኃይል አዛዥ የሆኑት ጄነራል ሥልጣናቸውን ለቀቁ

    በአፍሪካ እና በአውሮፓ የሚገኘው የአሜሪካ የምድር ኃይል እንዲሁም የኔቶ ምድር ኃይል አዛዥ የሆኑት ጄነራል ክሪስቶፈር ዶናሂው ኃላፊነታቸውን በይፋ ለቀቁ።

    ከአንድ ዓመት በላይ በኃላፊነቱ ላይ የቆዩት ጄነራል መልቀቃቸው የታወቀው ከሳምንት በፊት ቢሆንም በይፋ የተሰናበቱት ትናንት ሐሙስ ነው።

    የአሜሪካ ሠራዊት ጄነራሉ ከኃላፊነት የወረዱበት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን አልገለጸም። ለቦታው ተተኪ እስኪሾም ድረስ ሜጀር ጄነራል ክሪስቶፈር ኖሬዬጋ በአፍሪካ እና በአውሮፓ የሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎችን በተጠባባቂነት እንደሚመሩ ተገልጿል።

    የጄነራል ክሪስቶፈር ዶናሂው ከኃላፊነት መልቀቅ የታወቀው የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት በጦር ኃይሉ ከፍተኛ አዛዦች ላይ መጠነ ሰፊ ለውጥ ማካሄድ መጀመራቸውን ተከትሎ ነው። ባለ አራት ኮከብ ጄነራሎች ዝቅ ብለው ባለ ሦስት ኮከብ አዛዥ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ተገልጿል።

    አሁን ኃላፊነታቸውን የለቀቁት ጄነራል ወደ አፍሪካ እና አውሮፓ የአሜሪካ የምድር ኃይል አዛዥነት ከመምጣታቸው በፊት 18ኛውን አየር ወለድ ጓድን እንዲሁም 82ኛው አየር ወለድ ክፍልን መርተዋል።

    ጄነራሉ በተለይ የሚታወቁት የአሜሪካ ኃይሎች በ2021 አፍጋኒስታንን ለቅቀው ሲወጡ የመጨረሻው የአሜሪካ ወታደር በመሆናቸው ነው።

  7. እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተው የኢራን የታገደ ሀብት የት ነው ያለው?

    ከየካቲት አንስቶ በአሜሪካ እና በእስራኤል የተከፈተባት ጦርነትም ኢኮኖሚውን ይበልጥ ጫና ውስጥ ከትቶታል።

    ይሁን እንጂ በዕግድ ላይ ባለው የኢራን ሀብት ጉዳይ ባለበት የሕግ፣ የፋይናንስ እንዲሁም ፖለቲካዊ እንቅፋቶች የተነሳ ገንዘቧን ለማስለቀቅ የተፈረመው ስምምነት ወደ ተግባር ለማውረድ ጊዜ የሚወስድ እና ውስብስብ ሂደት መሆኑ አይቀርም።

    እነዚህ ሀብቶች በትክክል ምንድናቸው? የኢራንስ ምን ያህል በቀላሉ ልታገኘው ትችላለች? ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተው የኢራን የታገደ ሀብት የት ነው ያለው?

  8. ኢራን በቀድሞው ጠቅላይ መሪ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት እንዳይፈጽሙ አስጠነቀቀች

    የካቲት ላይ በተፈጸመው የመጀመሪያ ጥቃት ለተገደሉት የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ለማካሄድ እየተዘጋጀች ያለችው ኢራን፤ አሜሪካ እና እስራኤል ማንኛውም ጥቃት እንዳይሰነዝሩ አስጠነቀቀች።

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከሐሙስ እስከ ቅዳሜ ድረስ በኢራን እና ኢራቅ ውስጥ የተለያዩ ስፍራዎች እንዲካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የበርካታ አገራት ባለሥልጣናትም በሥነ ሥርዓቱ ለመታደም ወደ ቴህራን እንደሚጓዙ አስታውቀዋል።

    ቻይና፣ ፓኪስታን፣ ሕንድ እና ኳታር ባለሥልጣናቶቻቸውን ከሚልኩ አገራት መካከል ተጠቅሰዋል። ጦርነቱን ለመቋጨት አሸማጋይ የሆነችው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ የአያቶላህ ኻሜኒን ቀብር ለመታደም ወደ ኢራን እንደሚጓዙ መንግሥታቸው ገልጿል።

    ለቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወደ ኢራን ለሚመጡ “ሁለት ሺህ” የአፍጋኒስታን ዜጎች ቪዛ እንደተሰጠም ቢቢሲ ፐርሺያ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

    ይህ ዝግጅት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ኻታም አል አንቢያ በመባል የሚታወቀው የኢራን ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ማዘዣ የማስጠንቀቂያ መግለጫ ማውጣቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ዋና አዛዡ አሊ አብዶላህ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈ መግለጫቸው፤ “የኢራንን ጠላቶች በተለይም አሜሪካን እና ጽዮናዊውን ሥርዓት (እስራኤል) ከማንኛውም የተሳሳተ ስሌት እንዲቆጠቡ” አስጠንቅቀዋል።

    “አገራችን ላይ ለሚቃጣ ማንኛውም ስጋት እና ጥቃት በጦር ኃይሎቻችን ስለሚሰጠው ከባድ የአጸፋ እርምጃ እንዲያስቡ እናስጠነቅቃለን” ሲሉም አሳስበዋል።

    ረቡዕ ዕለትም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፤ በአገሪቱ ሕዝብ ወይም አመራር ላይ ለሚሰነዘር ማንኛውም ስጋት አፋጣኝ እና ጠንካራ ምላሽ እንደሚሰጥ በመግለጽ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።

    አራግቺ ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጡት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ የአሁኑ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ “ለሞት የታጩ ናቸው” የሚል አስተያየት ከሰጡ በኋላ ነው።

    በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ከፍተኛ የደኅንነት እርምጃዎች እንደሚተገበሩ እንዲሁም በበርካታ ከተሞች ጊዜያዊ የአየር ክልል እገዳ እንደሚጣል መገለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።

  9. ዜጋዬ ተገድሏል ያለችው ጋና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ ገባች

    አንድ ጋናዊ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ካለው ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ተገደለ መባሉን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ተቀስቅሷል።

    የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጋው ኬፕ ታውን ውስጥ በመገደሉ ይፋዊ ተቃውሞውን እና ለፖሊስ አቤቱታ ማቅረቡን ገልጿል።

    የደቡብ አፍሪካ የፍትሕ ሚኒስትር ግን “የጋና ባለሥልጣናት መደበኛ ካልሆኑ ስደተኞች ጋር በተያያዘ ባለው ሁኔታ ላይ የሐሰት መረጃዎችን እያስተላለፉ ነው” ሲሉ ተቃውሞ አሰምተዋል።

    የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በበኩሉ ተገደለ ስለተባለው ጋናዊ መረጃ እንደሌለው፤ ነገር ግን ከወንጀል ጋር በተያያዘ ስለተገደለ ሌላ ጋናዊ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አሳውቋል።

    የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን የሆኑት ክሌይሰን ሞንዬላ ከፀረ ስደተኞች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ጋናዊ ተገድሏል መባሉን “የፈጠራ ታሪክ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ጋና በዜጋዋ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በመቃወም ባወጣችው መግለጫ “የማንንም ሕይወት መንጠቅ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት በመሆኑ ተጠያቂዎቹ በአፋጣኝ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው” ስትል ጠይቃለች።

    "የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት በግድያው ዙሪያ ፈጻሚዎቹ ተይዘው ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚደያርግ ሙሉ፣ ግልጽ እና ፈጣን ምርመራ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን” ብሏል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ።

    የጋና አንድ ሬዲዮ ጣቢያ እንደዘገበው የተገደለው ጋናዊ ለ20 ዓመታት ያህል በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የኖረ የልብስ ስፌት ባለሙያ እየነበረ ሲሆን በተቃዋሚዎች በጥይት ተገድሏል። አስከሬኑን ወደ አገሩ ለመውሰድ በጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ጥረት እየተደረገ ነው።

    ባለፈው ማክሰኞ ፀረ ስደተኞች ተቃዋሚዎች አፍሪካውያን ስደተኞች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው እንዲወጡ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ የነበረ ሲሆን፣ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።

    ጋና፣ ማላዊ እና ናይጄሪያ ከቀነ ገደቡ በፊት የተወሰኑ ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ ካስወጡ አገራት መካከል ናቸው። እስካሁን 25 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው ወጥተዋል።

  10. ሩሲያ በኪየቭ ላይ በፈፀመችው መጠነ ሰፊ ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች ተገደሉ

    የሩሲያ ኃይሎች በኪየቭ ላይ በፈጸሙት መጠነ ሰፊ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች ተገደሉ።

    በጥቃቱ ከተገደሉት በተጨማሪ 90 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

    የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል አብዛኞቹ ሕፃናት እንደሆኑ የኪየቭ የጦር አስተዳደር ኃላፊ ታይሙር ቲካቼንኮ ተናግረዋል።

    በርካታ ነዋሪዎችም ተፈናቅለዋል።

    ጥቃቱ ከ11 ሰዓታት በላይ እንደዘለቀ የተነገረ ሲሆን፣ በኪየቭ የሚገኘው የቢቢሲ ቡድን ረቡዕ ምሽት ከባድ ፍንዳታዎችን ሰምቷል።

    የከተማዋ ከንቲባ ቫታሊ ክሊትሽኮ ጥቃቱን በዩክሬን መዲና ላይ የተፈጸመ “እጅግ ከባድ ጥቃት” ያሉት ሲሆን፣ አርብ ዕለት የሀዘን ቀን እንዲሆን አውጀዋል።

    በጥቃት ከተመቱ ሥፍራዎች መካከል የአምቡላንስ ጣቢያ እንደሚገኝበትም ከንቲባው ገልጸዋል።

    ዩክሬን የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያን ዒላማ በማድረግ ሩሲያን ከስሳለች።

    ሞስኮ በበኩሏ በሩሲያ የሲቪል መሠረተ ልማት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት አፀፋ “የጦር መሣሪያ ማምረቻ ነው” ባለችው ላይ እርምጃ መውሰዷን ገልጻለች።

    የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲመትሪ ፔስኮቭ ሐሙስ ዕለት "ሩሲያ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት በኪየቭ መንግሥት ላይ የምታደርገውን ጫና እንደምትጨምር" ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    የዩክሬን አየር ኃይል እንዳለው ሩሲያ በረቡዕ ምሽቱ ጥቃት 74 ሚሳዔሎችን እና 496 ድሮኖችን አስወንጭፋለች።

    ሆኖም አብዛኞቹ በአገሪቷ የአየር ጥቃት መከላከያ መክሸፋቸውን እና 25 ባልስቲክ ሚሳዔሎች እና 12 ድሮኖች ብቻ በ33 ቦታዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አየር ኃይሉ ገልጿል።

  11. የኢራን ጠቅላይ መሪ ሚስት ቀብር የባለቤታቸው አስከሬን ባልተገኘበት ተፈጸመ

    በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት ከወራት በፊት የተገደሉት የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ባለቤት ዛሃራ ሃዳድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ባላቸው ባልተገኙበት ረቡዕ ዕለት ቴህራን ውስጥ መፈጸሙ ተዘገበ።

    ዛሃራ ሃዳድ አዴል በመጀመሪያው ዕለት ጥቃት ከተገደሉት የኻሜኒ ቤተሰብ አባላት አንዷ ናቸው። በመጀመሪያው ዕለት የቦምብ ጥቃት የኢራን ጠቅላይ መሪ እና ሌሎች በርካታ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገደላቸው ይታወሳል።

    በተጨማሪም የአባታቸውን ሥልጣን የተረከቡት የዛሃራ ባለቤት ሞጅታባ ኻሜኒ በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው በተደጋጋሚ ቢነገርም እስካሁን በተጨባጭ የተረጋገጠ ነገር የለም።

    የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ ከሆኑ በኋላ የጽሁፍ መልዕክት ከማስተላለፍ ውጪ በይፋ ለሕዝብ ያልታዩት ሞጅታባ በጥቃቱ በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።

    በመጀመሪያው ዕለት ጥቃት የተገደሉት የሞጅታባ ሚስት ዛሃራ የሟቹ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አማካሪ እና በእስላማዊው ሪፐብሊክ ውስጥ ተደማጭ የሆኑት ጎላማሊ ሃዳድ አዴል ልጅ ነበሩ።

    ከጥቂት ቀናት በፊት ጎላማሊ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ ወዲህ የሟች ሴት ልጃቸው ባለቤት የሆኑትን ሞጅታባ ኻሜኒን አግኝተዋቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

  12. “የሆርሙዝ ወሽመጥ የኢራን የማያሻማ ሉዓላዊ ግዛት አካል ነው” - የኢራን ጦር

    ሆርሙዝ ወሽመጥ የማያሻማ የኢራን ሉዓላዊ የውሃ አካል በመሆኑ ለወራሪዎች ቦታ እንደሌለው ኻታም አል-አንቢያ በመባል የሚታወቀው የኢራን ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ማዘዣ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

    ስለዚህም “ከአሜሪካ በኩል በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረግ የትኛውም ዓይነት ጠልቃ ገብነት ከኢራን ጦር ኃይሎች ፈጣን እና የማያዳግም ምላሽ ይሰጠዋል” በማለት አስጠንቅቋል።

    ከማዘዣ ማዕከሉ የወጣውን መግለጫ ጠቅሰው የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት “ወሳኝ የውሃ ላይ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነት እና አስተዳደር ጉዳይ የኃያላኑ የእስላማዊት ኢራን ጦር ኃይሎች የማይታለፍ ቀይ መስመር ነው” በማለት አጽንኦት መስጠቱን አመልክተዋል።

    “ሆርሙዝ ወሽመጥ የወራሪዋ አሜሪካ የምትቆጣጠረው መስክ ሳይሆን፣ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የማያሻማ ሉዓላዊ ግዛት ነው” ሲል ኢራን በባሕር መተላለፊያው ላይ ያላትን የበላይነት ገልጿል።

    ሁሉም የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሰላም ለማለፍ በኢራን የተቀመጠውን መስመር ብቻ መከተል እንዳለባቸው እና ካልሆነ ግን የሚገጥማቸውን ቅጣት መቀበል እንደሚገባቸው አስጠንቅቋል።

    ኢራን በአሜሪካ እና በእስራኤል ጦርነት ከተከፈተባት በኋላ በወሳኙ የባሕር መስመር በኩል ላይ በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር በመጀመሯ ሆርሙዝ ዝግ ሆኖ ቆይቷል።

    ሆርሙዝ ከዓለም ፍጆታ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው ነዳጅ እና ጋዝ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤው አገራት በመነሳት የሚተላለፍበት ወሳኝ የባሕር መስመር ነው። በጦርነቱ ወቅት መርከቦች ማለፍ ባለመቻላቸው በዓለም ዙሪያ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ ነበር።

  13. አሜሪካ ጦሯን ከሳዑዲ አረቢያ ለማስወጣት እያሰበች እንደሆነ ተዘገበ

    አሜሪካ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኝ ጦሯን ለመቀነስ ወይም የተወሰነውን ወታደራዊ ኃይል ከሳዑዲ አስወጥታ ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር እያሰበች እንደሆነ ዋል ስትሪት ጆርናል የተመለከተውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገበ።

    አሜሪካ ይሄንን እርምጃ ለመውሰድ እያሰበች ያለው በዋሽንግተን እና በሪያድ መካከል ያለውን ውጥረት ተከትሎ ነው ተብሏል።

    ሁለቱ አገራት በኢራን ጦርነት እንዲሁም በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ደኅንነት ከማስጠበቅ ጋር በተያያዘ ውጥረታቸው ተባብሷል።

    ዋል ስትሪት ጆርናል የተመለከተው ሪፖርት እንደሚጠቁመው፤ ከ100 በላይ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ የጦር ሰፈሮች እና ከወታደራዊ መርከቦች በመነሳት በረራ አድርገዋል።

    ይህ ስምሪት ከሳዑዲ አረቢያ ያልተጠበቀ መሰናክል እንደገጠመው ዘገባው ያትታል።

    በሳዑዲ የሚገኙ የጦር ሰፈሮች እና የአገሪቱ የአየር ክልል ለዚህ ስምሪት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ቢሆንም ሪያድ ከዋሽንግተን ጋር ለመተባበር አልፈቀደችም።

    ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለዋል ስትሪት ጆርናል እንደገለጹት፤ የሳዑዲ ተቃውሞ አሜሪካ ‘ኦፕሬሽን ፕሮጀክት ፍሪደም’ የተባለውን ስምሪት እንድታቋርጥ አስገድዷታል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ ያደረጉት ኦፕሬሽን መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲተላለፉ ለማስቻል ያለመ ነበር።

    አሜሪካ ኦፕሬሽኑን ያቋረጠችው በግማሽ ልብ ሆና ነው ተብሏል።

    አሜሪካ በሳዑዲ ያላትን ጦር ለመቀነስ አልያም የተወሰነ ወታደራዊ ኃይሏን ከሳዑዲ አስወጥታ ወደ እስራኤል ወይም ዮርዳኖች ለማዘዋወቅ ማሰቧን የዋል ስትሪት ዘገባ ይገልጻል።

    በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰም ዘገባው ያትታል።

    አሜሪካ ወታደሮቿን ለማስወጣት ከመወሰኗ በፊት አማራጮችን እንደምትመለከትም ተገልጿል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት ስለ ጉዳዩ ማረጋገጫም ማስተባበያም አልሰጡም።

  14. ሆርሙዝ በአሜሪካ ሳይሆን በኢራን ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ መታወቅ አለበት - ኢራን

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ሳይሆን በኢራን ቁጥጥር ሥር ነው ሲሉ የአገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ገለጹ።

    የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ በኢራን ላይ የሚካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ የሚመራ ሲሆን፣ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር እና በኢራን ላይ እስካሁን የተፈጸሙ ጥቃቶችን የሚያስተባብር አካል ነው።

    ‘ሴንትኮም’ የተባለው ይህ ወታደራዊ ዕዝ በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ወሽመጥ ላይ ዋነኛ ኃይል ነው። ነገር ግን የኢራን ጦር በአካባቢው ባለው ሉዓላዊነት የተነሳ በቀጣናው መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ ለማገድ ችሎ ቆይቷል።

    በዚህም የተነሳ ኢራን በመተላለፊው ላይ ያላትን ቁጥጥር ለማጥበቅ ሕግ እስከማውጣት ደርሳለች። ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ከአሜሪካ ጋር እየተካሄደ ያለው ንግግር ኢራን በሆርሙዝ ላይ ያላትን የበላይነት አሳልፎ የሚሰጥ አለመሆኑን አስረግጠው ገልጸዋል።

    ጋሪባባዲ ጨምረውም "ባህሬን ውስጥ የሚካሄደው ወታደራዊ ውይይት የባሕረ ሰላጤውን ደኅንነት የተመለከተ ሕጋዊ አሠራርን የሚፈጥር አይደለም። ከዚያ ይልቅ የቀጣናው ደኅንነት የሚረጋገጠው የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ሲያበቃ እና ከአካባቢው ስትወጣ፣ የአገራት ሉዓላዊነት ሲከበር እንዲሁም ከአሜሪካ የበላይነት ውጪ አዲሱን ጂኦፖለቲካዊ እውነታን በመቀበል ነው” ብለዋል።

    ባለፉት ወራት ተዘግቶ ቆይቶ ከሳምንት በፊት የተከፈተው ሆርሙዝ ወሽመጥ አሁንም ደኅንነቱ የተጠበቀ ባለመሆኑ ማኅበራት እና የመርከብ ኩባንያዎች መተላለፊያው “የጦርነት ቀጣና” ሆኖ መታየቱ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።

    ሆርሙዝ መጀመሪያ ላይ በዚህ ምደባ ውስጥ የተካተተው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ከቀናት በኋላ በመርከቦች ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ነበር። አሁንም በመርከቦች ላይ አልፎ አልፎ ጥቃቶች እየተፈጸሙ በመሆናቸው ነው ስጋቱ የተፈጠረው።

  15. ኢራን እና አሜሪካ ውይይት ለመቀጠል መስማማታቸውን ኳታር ገለጸች

    በኳታር ዶሃ ሲካሄድ የነበረው የኢራን እና የአሜሪካ ልዑካን ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት መጠናቀቁን የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጂድ አል-ናስሪ ተናግረዋል።

    “ተደራዳሪዎቹ ምክክር እና ውይይት ለመቀጠል ተስማምተዋል። ቀጣዩ ውይይት መቼ እንደሚካሄድ በተቻለ ፍጥነት የሚገለጽ ይሆናል” ብለዋል።

    ውይይቱ “በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ” መሆኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በፓኪስታን እና በኳታር አሸማጋዮች በኩል የተደረገውን ንግግር “እጅግ ጥሩ ስብሰባ” ሲሉ ገልጸው “ለውጥ እየታየበት ነው” ብለዋል።

    ቴህራን ወደ ውይይት ወይም ድርድር ለመመለስ ዕቅድ እንዳልያዘች ገልጻ የነበረ ቢሆንም፤ ከአሜሪካ ልዑካን ጋር ቀጥተኛ ባልሆነ ውይይት ላይ ልዑካኖቿ መላኳ ተገልጿል።

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባልባዲ በዶሃው ውይይት “የተቆጣጣሪው ቡድን ቀጥተኛ የግንኙነት መስመር ነገ እንዲከፈት” ተስማምተናል ብለዋል።

    “የመግባቢያ ሰነዱ ጥሰት በይፋ ይመዘገባል፣ ውይይት ይደረግበታል፣ ውሳኔም ይሰጥበታል” ሲሉም አክለዋል።

  16. “በዲፕሎማሲው ወይም በጦርነቱ የማታግዙን ከሆነ አታስቸግሩን”- የኢራን ባለሥልጣን

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ ከአገራቸው የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከአሜሪካ ጋር ስለሚደረገውን ድርድር ከቴህራን የሚነሱ ውስጣዊ ትችቶችን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “በዲፕሎማሲው ወይም በጦርነቱ የማታግዙን አታስቸግሩን” ብለዋል።

    በቃለ ምልልሱ ላይ ከኢራን የሚነሱ ውስጣዊ ትችቶችን በተመለከተ ጠንካራ ንግግሮችን አድርገዋል።

    ስዊትዘርላንድ በተደረገው ድርድር፤ እገዳ ተጥሎበት የነበረውን የኢራን ሃብት የሚያስመልስ ሰነድ መጠናቀቁን ገልጸዋል። በዚህ ውይይት ላይ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እንዲሁም የአሜሪካ ግምጃ ቤት ምክትል ጸሐፊ መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

    ከአሜሪካ ጋር ስለሚደረገው ድርድር እና ስለ ተደራዳሪው ቡድን የሚነሱ የአገር ውስጥ ትችቶችን በተመለከተ ደግሞ “በዲፕሎማሲው ወይም በጦርነቱ የማታግዙን ከሆነ አታስቸግሩን፤ የትራምፕን ንግግር መድገም አቁሙ. . . በጎ አይደለም። ሕዝቡ እንዲረጋጋ እና በኢስላሚክ ሪፐብሊኳ ደስተኛ እንዲሆን ተውት” ብለዋል።

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ተወካዮች ወደ ኢራን የመግባታቸውን ጉዳይ በተመለከተ “በምክር ቤት ባስተላለፍነው ውሳኔ እና ጠቅላይ የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስሉም ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን በማንኛውም ሁኔታ መመልከት አይቻለም” ብለዋል።

    በሌላ በኩል አሜሪካ እና ኢራን በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ እያደረጉ ያሉት ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር “በጥሩ ሁኔታ” እየተካሄደ መሆኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገልጸዋል።

  17. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ እና ኢራን ተደራዳሪዎች ንግግር በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ተናገሩ

    አሜሪካ እና ኢራን በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ እያደረጉ ያሉት ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ በፓኪስታን እና በኳታር አሸማጋዮች በኩል የሚደረገውን ንግግር “እጅግ ጥሩ ስብሰባ” ሲሉ ገልጸውታል።

    ወደ ሰሜን ዳኮታ ግዛት ከመብረራቸው በፊት ከጋዜጠኞች ጋር የተነጋገሩት ትራምፕ፤ “ኢራንን ከኒውክሌር ነጻ የማድረግ ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው” ብለዋል።

    የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የመገንባት ዕቅድ አላት የሚል ክስ የሚቀርብባት ኢራን፤ የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ እንደሚል በተደጋጋሚ ገልጻለች።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ “በጣም ጥሩ ስብሰባዎችን አድርገዋል፤ [የሚሆነውን] እናያለን” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። “እጅግ በኃይለኛው መትተናቸዋል…ሆኖም በጣም በጥሩ ሁኔታ እየተቀራረብን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

    ኳታር ውስጥ እየተደረገ ባለው ቴክኒካዊ ንግግር ላይ የአሜሪካ እና ኢራን ባለሥልጣናት ፊት ለፊት ለድርድር አልተቀመጡም።

    የአሜሪካ ዋነኛ ተደራዳሪ የሆኑት የፕሬዝዳንቱ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የ ትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር ወደ ዶሃ ተጉዘዋል።

    የሁለቱ አገራት ተደራዳሪዎች ንግግር ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን ተኩስ ልውውጥ ተከትሎ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የሚያስችሉ ነጥቦችን በአሸማጋዮች አማካኝነት አንዳቸው ለሌላቸው ያቀርባሉ።

  18. የሜክሲኮ ብሔራዊ ቡድን በማሸነፉ አደባባይ ከወጡ ደጋፊዎች ሦስቱ ሕይወታቸው አለፈ

    በዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ኢኳዶርን የገጠመችው ሜክሲኮ በአሸናፊነት ወደ ቀጣዩ ዙር በማለፏ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ከወጡ የአገሪቱ ዜጎች መካከል የሦስቱ ሕይወት አለፈ።

    ደጋፊዎቹ ሕይወታቸው ያለፈው፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ በወጡባት ዋና ከተማዋ ሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ በተፈጠረው መገፋፋት ነው። ሕይወታቸው ያለፈው የ19 እና የ48 ዓመት ሴቶች እና የ44 ዓመት ወንድ ናቸው።

    የከተማዋ የጤና ባለሥልጣናት እንዳሉት የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን ስተው የነበሩትን ሦስቱን ሰዎች ለመርዳት ሙከራ ከተደረገ በኋላ ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሆስፒታል ተልከው ሕይወታቸው እዚያ አልፏል።

    ከአሜሪካ፣ ከካናዳ ጋር በጋራ የዓለም ዋንጫን እያስተናገደች ያለችው ሜክሲኮ ኢኳዶርን ሁለት ለዜሮ በሆነ ውጤት ካሸነፈች በኋላ የአገሪቱ ዜጎች በደስታ ሰክረው ወደ አደባባይ ወጥተዋል።

    በሜክሲኳዊያን ዘንድ ይህ ከፍተኛ ደስታ የተፈጠረው አገራቸው ከአውሮፓውያን 1986 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጥሎ ማለፍ በመድረሷ ነው።

    ሦስት ሰዎች የሞቱበት ሁኔታ ከተከሰተ በኋላ የሜክሲኮ ሲቲ ከንቲባ ክላራ ብሩጋዳ ሕይወታቸው ላለፈ ሰዎች ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ገልጸው፣ የአገሪቱ ዜጎች ደስታቸውን ሲገልጹ “በኃላፊነት እና በጥንቃቄ” እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

    ሜክሲኮ 32 ቡድኖች ከሚገኙበት ጥሎ ማለፍ በመሻገር ወደ 16ቱ ምድብ ተቀላቅላለች። በቀጣይ ደግሞ ዛሬ ረቡዕ ምሽት እንግሊዝ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ በሚያደርጉት ጨዋታ ከሚያሸንፈው ቡድን ጋር ትጋጠማለች።

  19. በቬንዙዌላ መሬት መንቀጥቀጥ ለስድስት ቀናት ተቀብሮ የነበረ የሦስት ዓመት ልጅ በሕይወት ተገኘ

    በቬንዙዌላ ባጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ ለስድስት ቀናት ፍርስራሽ ውስጥ ተቀብሮ የቆየ የሦስት ዓመት ልጅ በሕይወት መገኘቱን በስፍራው እየተንቀሳቀሰ ያለ የነፍስ አድን ቡድን አስታወቀ።

    ክሊበር ሞራን የተባለ ህጻን ላ ጉዋይራ ግዛት ውስጥ ከፍርስራሽ ስር መውጣቱን የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ተናግረዋል። ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቷ የህጻኑን በሕይወት መገኘት "የሕዝባችን የጥንካሬ እና የተስፋ ምንጭ" ሲሉ ገልጸውታል።

    ባለፈው ሳምንት የተከሰቱት በሬክተር ስኬል 7.2 እና 7.5 ሆነው የተለኩ ሁለት የመሬት መንቀጥቀጦች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 1,943 አድጓል። ከ10,000 በላይ ሰዎች የተጎዱ ሲሆን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ያሉበት አልታወቀም።

    ከአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም የናሳ የተገኘ የሳተላይት መረጃ ላይ የተደረገ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ እንደሚያሳየው፤ በመሬት መንቀጥቀጡ 58,870 ገደማ ሕንጻዎች እንደተጎዱ ወይም ሙሉ በሙሉ እንደፈረሱ ተገምቷል።

    የሦስት ዓመቱን ልጅ ያገኘው የዮርዳኖስ ሲቪል መከላከያ ቡድን እንዳስታወቀው፤ ሕጻኑ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ተደርጎለት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል። የልብ ምት እና ስትንፋስን ጨምሮ መሰል መሠረታዊ የጤና ሁኔታው ጥሩ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

    በመሬት መንቀጥቀጥ የተቀበሩ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ በሕይወት የመገኘት ዕድል ያላቸው በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ውስጥ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገናራሉ። ሕጻኑ በሕይወት ከፍርስራሽ ስር የወጣው ከዚህ ጊዜ ከተጨማሪ ሦስት ቀናት በኋላ ነው።

    በመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ስፍራዎች አንዱ ላ ጉዋይራ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን ሰዎችን የማዳን ስራ ላይ ተሰማርተዋል።

    የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ላ ጉዋይራ ውስጥ መጠነ ሠፊ የምግብ እጥረት እንደተከሰተ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንደሌሉ እንዲሁም የኮሚዩኒኬሽን መስመሮች በከፍተኛ ደረጃ መቋረጣቸውን አስታውቋል።

  20. በፓኪስታን የሕጻናት ማሠልጠኛ ጣሪያ ተደርምሶ 14 ልጆች ሞቱ

    በፓኪስታን በሚገኝ የግል የሕጻናት ማሠልጠኛ ተቋም ጣሪያ ተደርምሶ 14 ልጆች መሞታቸው ተገለጸ።

    ጣሪያው ለምን እንደተደረመሰ ምርመራ የተከፈተ ሲሆን፤ በተቋሙ ውስጥ የነበሩት ሕጻናት ከ10 ዓመት በታች መሆናቸው ተገልጿል።

    ከክስተቱ ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    የድንገተኛ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጠው ሬስኪው 1122 ቃል አቀባይ ፋሩቅ አሕመድ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ሕጻናቱን ከሕንጻው ለማውጣት አንድ ሰዓት ወስዷል።

    ተጨማሪ አምስት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ይገመታል።

    ከተጎጂዎቹ አንዷ የእህቱ ልጅ እንደሆነች የገለጸ ግለሰብ ሕንጻው “ተዳክሞ” እንደነበር ተናግሯል።

    ልጆቹ እየተማሩ ሳለ ለሕንጻው ጥገና እየተደረገ እንደነበረም ገልጿል።

    “ድንገት ሕንጻው ተደረመሰ። የተወሰኑ ልጆች አናት ላይ ነው የወደቀው። ጣሪያውን ስለተጫኑት ተደርምሷል” ሲልም ክስተቱን ገልጿል።

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር በአደጋው የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።