አሜሪካ እና ኢራን የአያቶላህ ኻሜኒ ቀብር እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከድርድር እረፍት መውሰዳቸውን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር የምታደርገው ድርድር እየተካሄደ ያልሆነው ሁለቱ አገራት የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ስነ ስርዓት እስከሚጠናቀቅ ድረስ እረፍት ለመውሰድ በመወሰናቸው መሆኑን ለአክሲዮስ ተናገሩ።
ትራምፕ፤ በኻሜኒ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ የተወሰኑ ኢራናውያን ሲያለቅሱ በመመልከታቸው እንደተገረሙ ከአሜሪካው የዜና ምንጭ ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል። ሕዝቡ የቀድሞውን ጠቅላይ መሪ ይጠላቸዋል ብለው ያስቡ እንደነበር የተናገሩት ትራምፕ፤ "ምናልባት የውሸት እንባ ሊሆን ይችላል" ማለታቸው ተዘግቧል።
አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት ወር ኢራን ላይ በፈጸሙት ጥቃት የተገደሉትን አያቶላህ ኻሜኒ ለመሸኘት ለሳምንት ገደማ የሚቆይ የቀብር ስነ ስርዓት ቴህራን ውስጥ መካሄድ ጀምሯል። ትናንት ቅዳሜ በተካሄደው የመጀመሪያ ቀን ስነ ስርዓት ላይ ጥቁር የለበሱ በርካታ ሐዘንተኞች ከቴህራን ዋና መስጊድ ውጪ ተሰብስበው ታይተዋል።
የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን በታላቁ ሞሳላ መስጊድ ውስጥ ያረፈ ሲሆን ግብዓተ መሬቱ የሚፈጸመው ሐሙስ ዕለት በትውልድ ከተማቸው ማሻድ ውስጥ ነው።
በቀጣዮቹ ቀናት ኢራን እና ኢራቅ ውስጥ በሚካሄደው የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የቴህራን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለ ቀብር ስነ ስርዓቱ ሲገናሩ፤ “ሁሉም እዚያው ናቸው። በአንድ ተኩስ [ሁሉንም ልንገድላቸው እንችላለን]። ነገር ግን ይህንን አናደርግም፤ ምክንያቱም የምንደራደረው ሰው አይኖርም" ብለዋል።
የኢራን ባለሥልጣናት “ስምምነት ላይ ለመድረስ እየለመኑ ነው” ሲሉ ከዚህ ቀደም የተናገሩትን የደገሙት ትራምፕ፤ ሁለቱም ወገኖች የኻሜኒ የቀብር ስነ ስርዓት እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለሳምንት ያህል ከድርድሩ እረፍት ለመውሰድ መወሰናቸውን ተናግረዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙም አክለዋል።
በተጨማሪም ትራምፕ በቀጣዩ ሳምንት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር ሊገናኙ እንደሚችሉ ለአክሲዮን ገልጸዋል። "እጅግ በጥሩ ሁኔታ እየተጓዝን ነው። [ኔታንያሁ] ማን አለቃ እንደሆነ ያውቃል" ማለታቸውን የዜና ምንጩ ዘግቧል።