ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ጥያቄ መሠረት ነገ ዶሃ ውስጥ ንግግር ይደረጋል አሉ
የአሜሪካ እና ኢራን ባለሥልጣናት ነገ ኳታር ውስጥ ለድርድር እንደሚገናኙ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ፤ “ኢራን ስብሰባ እንዲደረግ ጠይቃለች። ነገ ዶሃ ውስጥ ይካሄዳል” ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ነገ ማክሰኞ ይካሄዳል ስላሉት ስብሰባ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጡም።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ግን ዋነኞቹ የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ጃሬድ ኩሽር እና ስቲቭ ዊትኮፍ “በዚህ ሳምንት ዶሃ ውስጥ የሚካሄድ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ዶሃ እንደሚበርሩ” ለፎክስ ኒውስ ተካግረዋል።
ከዚህ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባ ጎን ለጎን የቴክኒካል ንግግር እንደሚካሄድም አክለዋል።
የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ ግን ዛሬ በሰጡት አስተያየት ሁለቱ አገራት በዚህ ሳምንት ቴክኒካዊ ንግግር ለማድረግ ዕቅድ ይዘዋል መባሉን አስተባብለው ነበር።
የኢራን ቴክኒካዊ ድርድር ቡድን ኃላፊ የሆኑት ጋሪባባዲ “የሌላኛውን ወገን ግዴታዎች አፈጻጸም መከታተልን ጨምሮ ከኳታር ጋር የሚደረጉት ምክክሮች ቢቀጥሉም፤ የሥራ ቡድኖቹ ቴክኒካዊ ንግግር ዶሃ ውስጥ ይካሄዳል በሚል በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የተሠራጨው ዘገባ ግን የተረጋገጠ አይደለም” ብለዋል።
የኢራኑ ባለሥልጣን ይህንን ከማለታቸው አስቀድሞ የተወሰኑ መገናኛ ብዙኃን ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ዋቢ በማድረግ፤ ቴህራን እና ዋሽንግተን የሚፈጽሟቸውን የአጸፋ ጥቃቶች ለማቆም እና ድርድሩን ለመቀጠል መስማማታቸውን ዘግበው ነበር።
የአሜሪካዎቹ የዜና ምንጮች ሲኤንኤን እና አክሲዮስ ደግሞ የቴክኒካዊ ድርድሩ ቀጣይ ክፍል ነገ ማክሰኞ ኳታር ውስጥ እንደሚካሄድ አስነብበው ነበር።
እነዚህ ዘገባዎች የወጡት አሜሪካ እና ኢራን አንዳቸው ሌላኛቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደጣሱ በመግለጽ ክስ ሲያሰሙ ከቆዩ በኋላ ነው። ባለፉት ቀናት በሆርሙዝ ወሽመጥ ውስጥ እና በዙሪያው በርካታ ጥቃቶች የተፈጸመዋል።