በአያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት “እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች” ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ
በቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት የመጀመሪያ ቀን በርካቶች ታድመዋል።
የኻሜኒ አስከሬን ባለበት የቴህራን ትልቁ መስጊድ የተገኙት ሰዎች ጥቁር በጥቁር ለብሰው ሐዘናቸውን እየገለጹም ነው።
የኢራን ባለሥልጣናት እንዳሉት በኢራን እና በኢራቅ ለቀናት በሚካሄደው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ “ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን” የሚደርሱ ሰዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።
በርካታ የኢራን መንግሥት ደጋፊዎች ዛሬ ቅዳሜ አደባባይ ወጥተው ለኻሜኒ ግድያ አሜሪካ ላይ የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቁ መፈክሮች አሰምተዋል።
የ37 ዓመቱ ፕ/ር ረዛ “ወደ ቀብር ሥነ ሥርዓቱ የመጣነው ከጠቅላይ መሪው ጋር እስከመጨረሻው አብረን ለመቆም ቃል ስለገባን ነው” ሲል ለኤኤፍፒ ተናግሯል።
“ለረዥም ጊዜ ራሳችንን ለጠቅላይ መሪው ስንል መስዋዕት እንደምናደርግ ተናግረናል። እሳቸው ግን ለእኛ ሲሉ መስዋዕት ሆኑ” በማለትም አክሏል።
የ40 ዓመቱ አራሽ ራሐሚ ደግሞ “ሁሉም እዚህ የመጣው የጠቅላይ መሪውን ሞት ለመበቀል ነው” ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል።
ከአራት ወራት በፊት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምሩ ነበር ኻሜኒ የተገደሉት።
ቀብራቸው የሚፈጸመው በትውልድ ከተማቸው ማሻሀድ የፊታችን ሐሙስ ይሆናል። እስከዚያም አስከሬናቸው በቴህራን በሚገኘው ግራንድ ሞሳላ መስጊድ ይቆያል።