የኢትዮ ቴሌኮም 40% ድርሻ ለሽያጭ ሲቀርብ፣ ለሦስተኛ የቴሌኮም ተቋም ጥሪ ቀረበ

ታትሟል

የኢትዮጵያ መንግሥት ግዙፉ የመንግሥት የልማት ድርጅት የሆነውን የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለሽያጭ ለማቅረብ ጨረታ አወጣ።

የገንዘብ ሚንስቴር የኢትዮ ቴሌኮምን የተወሰነ ድርሻ ወደ ግል ለማዞር ባለው ዕቀድ መሠረት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ተቋማት ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ጥሪ መቅረቡን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ እና ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻን ለግሉ ዘርፍ ለማስተላለፍ ጨረታ ወጥቷል።

በተጨማሪም ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከሳፋሪኮም በተጨማሪ ለሦስተኛ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ፈቃድ ለመስጠት ተወዳዳሪዎች ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለሥልጣን ጥሪ አቅርቧል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ ከተካተቱት ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለግል ክፍት ማድረግ አንዱ ነው።

በዕቅዱ መሠረት ለበርካታ ዓመታት በአገሪቱ ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ሆኖ የቆየውን የኢትዮ ቴሌኮምን ከፍተኛውን የ55 በመቶው ድርሻ በመንግሥት ይዞ ስር የሚቆይ ሲሆን፣ 5 በመቶው ደግሞ ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ይቀርባል።

ኢትዮ ቴሌኮም በአገሪቱ ውስጥ በብቸኝነት የቴሌኮም አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ ካፒታሉ 400 ቢሊየን ብር መድረሱ ይነገራል።

ኢትዮ ቴሌኮም 110 ሚሊዮን ሕዝብ ያላትን የኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያን ተቆጣጥሮ የቆየ ሲሆን የስልክ፣ የኢንተርኔት እና የገንዘብ ዝውውር አገልግሎቶችን በዋናነት እየሰጠ፣ የተለያዩ ዘመናዊ አገልግሎቶችን እያስተዋወቀ ይገኛል።

ይህንን በኢትዮ ቴሌኮም ተይዞ የቆየውን የኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ ለመቀላቀል በጨረታ አሸንፎ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ታዋቂ የሆነው ኩባንያ ሳፋሪኮም ፈቃድ ማግኘቱ ይታወሳል።

የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየው በሳፋሪኮም ጥምረት የሚመራው የቴሌኮም ኩባንያ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ በሆነችው ኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል።

ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በኢትዮ ቴሌኮም ተይዞ የቆየው የአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍን የተቀላቀለው ሳፋሪኮም ባለፉት ወራት አስፈላጊዎቹን መሠረተ ልማቶች በመዘርጋት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ከ52 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች በመላው አገሪቱ እንዳሉት ይታመናል።

ዕድሜ ጠገቡ ኩባንያ ለደንበኞቹ የስልክ፣ የኢንተርኔትና ሌሎች የቴሌኮም አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኘ ሲሆን፣ ኩባንያውን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጉ ተወዳዳሪነቱን እና ትርፋማነቱን ከፍ ያደርገዋል የሚል ዕምነት ያላቸው አለ።

ከአራት ዓመት በፊት በመንግሥት ቁጥጥር ስር የቆዩ ተቋማትን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ለማድረግ መንግሥት ከወሰነ በኋላ፣ የቴሌኮም ዘርፍ በቀዳሚነት ክፍት መደረጉ ይታወሳል።

በዚህም በአንድ አገለግሎት ሰጪ ድርጅት ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ተይዞ ወደ ነበረው የቴሌኮም ዘርፍ ለመግባት በተደረገው ጨረታ ሳፋሪኮም አሸንፎ ከወራት በፊት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።