የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች በኤአይ ላይ ያላቸውን አቋም ደጋግመው የሚያጋሩት ለምንድን ነው?

የሜታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ማርክ ዙከርበርግ በቅርቡ በኤአይ ላይ ያላቸውን ራዕይ የሚገልጽ ጽሑፍ ያጋሩ የቴክኖሎጂ አለቃ ናቸው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የቅርብ ጊዜ ክስተት የሆነው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በሁለት የተለያዩ ጎራዎች ማከራከሩን እንደቀጠለ ነው።

በአንድ በኩል የፈጠራ አቅምን ያዳክማል፣ ሥራን ያሳጣል በሚል አሉታዊ ጎኑ እንደሚያመዝን የሚከራከሩ እንዳሉ ሁሉ በሌላ በኩል ደግሞ ለችግሮች መፍትሔ ይሰጣል በሚል በበጎ የተቀበሉት አሉ።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ቴክኖሎጂው እየተስፋፋ እና እየተበራከተ መጥቷል። የቴክኖሎጂ አለቆችም ማኒፌስቶዎቻቸውን በማጋራት ስለቴክኖሎጂው እየሰበኩ ነው።

ባለፈው ሳምንት ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ዋትስአፕ እና ትሬድስን የሚያስተዳድረው ሜታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ " ዘ ፊዩቸር ኢዝ ፎር ኤቭሪዋን" በሚል ርዕስ 6 ሺህ 500 ቃላት ያሉት ግልጽ ደብዳቤ አጋርተዋል።

አንዳንዶች ደብዳቤውን ሰው ሠራሽ አስተውሎት(ኤአይ) ይዞት የመጣውን ተስፋ የሚገልጽ ሆኖ ቢያገኙትም ለሌሎች ግን ግልጽ አይደለም።

የዙከርበርግ ማኒፌስቶ ኤአይ ለምን "የወደፊቱ ትልቅ ጉዳይ" እንደሆነ የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ሲሆን፣ የቴክኖሎጂ አለቃው ያስቀመጡት ራዕይ፣ የኤአይ መሪዎች በተለያየ መንገድ የገለፁትን እና "እየሰሩት ያለው የቴክኖሎጂ ምርት በታሪክ በጣም ወሳኙ" እንደሆነ የገለፁትን ሃሳብ የሚያስተጋባ ነው።

ይህ ማኒፌስቶን የማጋራት ልምድ የተጀመረው እአአ በ2023 ከቲታን ኔትስኬፕ መሥራቾች አንዱ የሆነው ማርክ አንድሪሰን ' ዘ ቴክኖ ኦፕቲሚስት ማኒፌስቶ' በሚለው 5 ሺህ ቃል የያዘ ጽሑፍ ሳይሆን እንደማይቀር ተገልጿል።

በዚህ ጽሑፉ "የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በሕይወት የሚያጋጥሙ ችግሮችን የመፍቻ መንገዶች ናቸው" ሲል ይሞግታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አንድሪሰን ማኒፌስቶውን ማጋራት የጀመረው "እየተሰራጩ ነው" ያላቸውን "ሐሰተኛ መረጃዎች" በመግለፅ ሲሆን አንባቢዎችም ይህንን እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርቧል።

"እድገት ሒደት ነው ብለን እናምናለን" የሚለው አንድሪሰን፣ ይህም ወደ ደኅንነት፣ የሕይወት ለውጥ እና እውቀት መጎልበት የሚመራ ነው" ሲል ጽፏል።

ዙከርበርግም በቅርቡ በጋራው ጽሑፍ፣ ስም ባይጠቅስም በመጪዎቹ ቴክኖሎጂዎች አሉታዊ ተፅዕኖ ላይ ያስጠነቀቁትን በመጠየቅ የአንድርሰንን ሃሳብ አስተጋብቷል።

"በበርካታ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ላይ የሚቀርበው ክስ በጥፋት የተሞላ እንደሆነ የሚገልጽ መሆኑ አስገራሚ ነው" ብሏል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትም ( አይኤምኤፍ) ኤአይ ወደ 40 በመቶ የሚጠጉ ሰዎችን ሥራ ሊያሳጣ እንደሚችል እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አለመመጣጠንን እንደሚያባብስም አስጠንቅቋል።

በእርግጥ ዙከርበርግም ይህንን አይክዱም፤ ወደፊት ሥራ አጥነት ሊኖር ይችላል ብለዋል።

ሆኖም " ሁሉም ሰው ኤአይ ብዙ ሥራዎችን እና የሰውን ልጅ ሚና ያሳጣል ብሎ እንደሚያስብ እና ያንን የወደፊት ሕይወት ለመገንባት እንደሚቸኩሉ አይገባኝም" ብለዋል።

የዙከርበርግ ኩባንያ ሜታ በኤአይ ላይ ለማተኮር ራሱን እያደራጀ ባለበት ወቅት ወደ 10 በመቶ የሚሆነውን ወይም ወደ ስምንት ሺህ የሚጠጋ የሰው ኃይል መቀነሱም የሚያስደንቅ አይደለም።

በቅርብ ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋራ የዙከንበርግ ማኒፌስቶም በኤአይ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ነው።

እአአ በ2024 የቻትጂፒቲ አምራች የሆነው የኦፕን ኤኤይ ኃላፊ ሳም አልትማን፣ 'ዘ ኢንተለጀንስ ኤጅ' የተሰኘ ማኒፌስቶ አውጥተዋል። ይህም ስለቴክኖሎጂው አቅም ሰፊ የሆነ የተስፋ መግለጫ የያዘ ነው።

ማኒፌስቶውን "የሰውን ልጅ እድገት በአስደናቂ ሁኔታ ለማፋጠን የተዘጋጀ ነው" ያሉት ሲሆን "በጥበብ፤ ግን በልበ ሙሉነት እርምጃ መውሰድ አለብን" ብለዋል።

በዚያው ዓመት 'ማሽን ኦፍ ላቪንግ ግሬስ" በሚለው ማኒፌስቶም የአንትሮፒክ ሥራ አስፈፃሚ ዳሪዮ አሞዲ፣ ኤአይ ከጤና እንክብካቤ ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ድረስ የመቀየር አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል።

በማኒፌስቷቸውም የኤአይን ጠቀሜታ ለማሳየት የሞከሩ ሲሆን እንደ አጥፊ መቆጠር እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

የአንትሮፒክ አለቃ ዳሪዮ አሞዴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአንትሮፒክ አለቃ ዳሪዮ አሞዴም በማኒፌስቷቸው በኤአይ ላይ ያላቸውን ራዕይ ገልጸዋል

የዙከርበርግ አዲሱ ማኒፌስቶም የኤአይ ቴክኖሎጂዎቹን በግልጽ ለማጋራት ዕቅድ እንዳለ አስታውቋል። ዕቅዱ ከቴክኖሎጂው ጀርባ ያለው ዲዛይን ወይም ኮድ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፤ ይህም ማንኛውም ሰው እንዲያየው፣ እንዲጠቀምበት እና እንዲቀይረው የሚያስችል ነው።

እነዚህ መሣሪያዎች ክፍት ምንጭ (ኦፕን ሶርስ) መሆን አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚለው ጉዳይ ውዝግብ ያስነሳ ሲሆን ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚል ስጋትም ፈጥረዋል።

በቅርብ ሳምንታት ውስጥም በርካታ የኤአይ ሞዴሎች ወደ ድረ ገጾች ገብተዋል።

እነዚህ ሞዴሎች ክፍት ምንጭ ሆነው የተሰሩ አይደሉም፤ ነገር ግን ቴክኖሎጂው እያደገ ሲሄድ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሱ ናቸው።

የምጣኔ ሃብት ጉዳይ ጦማሪው ኖህ ስሚዝ "ሰብዓዊነትን የመግደል አቅም ያለውን ነገር ክፍት ምንጭ ማድረግ አለብን?" ሲሉ ጥያቄ ሰንዝረዋል።

"በጥንቃቄ ካልወሰዳችሁት፤ ሞኞች ናችሁ" ሲሉም አክለዋል።

ክፍት ምንጭ (ኦፕን ሶርስ) ገበያው እንደ ክዊን፣ ዲፕሲክ እና ጂኤልኤም ባሉ የቻይና የኤአይ ሞዴሎች ቁጥጥር ሥር ባለበት በዚህ ወቅት ተጨማሪ ፍላጎት እያስገኘ ነው።

ተደጋግመው የሚወጡ የእነዚህ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ማኒፌስቶዎችም ሥራ አስፈፃሚዎች እራሳቸውን እና ኩባንያዎቻቸውን ገበያው ውስጥ ለማስገባት መንገድ ሆነው እያገለገሉ ነው።

በቱላን ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ፕሮሰፌር የሆኑት ሮብ ላልካ " ምን ያህል ብልህ እንደሆናችሁ የማሳያ መንገድ ነው" [በማኒፌዎስቶቻቸው] "አሻግረው የሚመለከቱት መጪው ዘመን ብሩህ መሆኑን ለማሳየት እየሞገቱ ነው" ብለዋል።

ላልካ እንዳሉት ዙከርበርግ ማኒፌስቶ ያወጡበት ወቅት ኤአይ ከሥራ እስከ አካባቢ ለውጥ ድረስ በሁሉም ነገር ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ላይ የሚነሳው ቁጣ በጨመረበት ወቅት ነው።

ማኒፌስቶዎቻቸውም "ቴክኖሎጂው የሕዝብ ተቃውሞ ከሚነሳበት አሉታዊ ጎኖች ይልቅ ጠቀሜታው እጅግ የላቀ መሆኑን ለማረጋገጥ እየሞከሩ ነው" ብለዋል ላልካ።

"ግን የቴክኖሎጂውን በጎ ጎን ለማየት የሚያስችሉ ምክንያቶች ገና አልታዩም ብዬ አስባለሁ።" ሲሉም አክለዋል።