ከሌላ ጥናታዊ ጹሑፍ ኮርጀዋል በሚል ተከስሰው የነበሩት የኬምብሪጅ ፕሮፌሰር ሞተው ተገኙ

ጄሰን አርዴይ ቃለ መተይቅ እየሰጡ

የፎቶው ባለመብት, ITV/Shutterstock

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ከሌላ ሰው ኮርጀዋል ተብለው ተከስሰው የነበሩት የቀድሞው የኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ጄሰን አርዴይ ሞተው ተገኙ።

አርብ ከሰዓት በደቡባዊ ለንደን ባተርሲያ ወደሚገኝ መኖሪያ ቤት የደረሱት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች "ራሳቸውን ስተው" እንዳገኟቸው አስታውቀዋል።

አርዴይ ከኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የለቀቁት ከሌላ ሰው ጥናታዊ ጽሑፍ ሰርቀዋል የሚል ውንጀላ ከቀረበባቸው እና የተወሰኑ ስኬቶቻቸው ላይ ጥያቄ ከተነሳባቸው በኋላ ባለፈው ሳምንት ነበር።

ፕሮፌሰሩ የቀረቡባቸውን ውንጀላዎች በሙሉ ውድቅ አድርገዋል።

የአርዴይ ቤተሰቦች ሞታቸው ከተሰማ በኋላ ባወጡት መግለጫ "ይህንን የመሰለ አባተ፣ አጋር፣ ወንድም፣ አጎት እና ልጅ በማጣታችን ድንጋጤ ውስጥ ነን።" ብለዋል።

አክለውም "መልካም እና ምንጊዜም በሁሉም ሰው ውስጥ መልካም ነገር ለማየት ይፈልግ ለነበረው ለጄሰን የተከፈተበት የሐሰት ዘመቻ ከባድ ነበር።" ሲሉ ተናግረዋል።

አርብ ዕለት ፖሊስ በባተርሲያ ወደሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ጥሪ ደርሶት ወደ ሥፍራው ማምራቱን አስታውቋል።

የሜትሮፖሊታን ፖሊስ ባወጣው መግለጫ "በአሁኑ ጊዜ ሞቱ ያልተጠበቀ እንደሆነ ተደርጎ ነው የተመዘገበው፤ ነገር ግን አጠራጣሪ ነገር ይኖራል ተብሎ አይገመትም" ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቻንስለር ፕሮፌሰር ዴቦራ ፕሬንቲስ "ይህንን አሳዛኝ ዜና በመስማታችን በጣም አዝነናል። በዚህ እጅግ አስቸጋሪ ወቅት ለጄሰን አርዴይ ቤተሰቦችና ጓደኞች የተሰማንን ከልብ የመነጨ ሐዘናችንን እንገልጻለን" ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ሉሲ ፓውል የፕሮፌሰሩን ሞት በሰሙበት ወቅት "በጣም እንደደነገጡ እና እንዳዘኑ" እንዲሁም ሰዎች "በሚወዷቸው ሰዎች የተከበቡ እውነተኛ ሰዎች እንዳሉ እንዲያስታውሱ" አሳስበዋል።

የ41 ዓመቱ አርዴይ ምንም ዓይነት የስርቆት ተግባር (ፕላጃሪዝም) አለመፈጸማቸውን በመግለጽ አስረድተው ነበር፤ ነገር ግን በሥራዎቻቸው ላይ ስህተቶችን መኖራቸውን አምነዋል።

ባለፈው ሳምንት በቅርቡ በሥራዎቻቸው ላይ የተነሳው ውዝግብ "ከበርካታ ሰዎች የማያቋርጥ ትችት እና ጥቃት" እንደደረሰባቸው ተናግረው ነበር።

በፕሮፌሰሩ ሥራዎች ላይ ጥያቄ መነሳት የጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 ከኬምብሪጅ የተባረሩት እና ራሳቸውን "ሬስ ሪያሊስት" ነኝ ብለው የሚጠሩት ናታን ኮፍናስ፣ በፕሮፌሰሩ ሥራ ውስጥ በርካታ ከሌላ ሰዎች ስራ ውስጥ ተወሰደው እንደራስ ተደርጎ የቀረቡ መረጃዎችን ማግኘታቸውን ከተናገሩ በኋላ ነው።

አርዴይ ግን ቀደም ሲል በሠሯቸው የምርምር ሥራዎች ውስጥ አንዳንድ ስህተቶች የተከሰቱት የኦቲዝም ታማሚ በመሆናቸው ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል።

አክለውም ተመሳሳይ ምርመራ በሌሎች ምሁራን ሥራዎች ላይ ቢደረግ ተመሳሳይ ስህተቶች እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለታይምስ ጋዜጣ "እዚህ ላይ ስለ አካዳሚክ ትምህርት እየተነጋገርን ነው። ማንንም አልገደልኩም። ያጋጠመኝ ጭካኔ እና እንደ ውሸታም እና ህልመኛ ተደርጌ መቆጠሬ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብዬ አስባለሁ" በማለት ተናግረው ነበር።

አርዴይ እአአ በ2023 በ37 ዓመቴ የኬምብሪጅ በዕድሜ ትንሹ ጥቁር ፕሮፌሰር ሆነው መሾማቸው በወቅቱ ከፍተኛ ውዳሴ አግኝቶ ነበር።

አርዴይ ባለፈው ሳምንት የሥራ መልቀቂያ ሲያስገቡ እየቀረበባቸው ያለው ትችት "በግል ሕይወቴ ላይ" "እጅግ ከባድ" ሆኗል ብለው ነበር።

"ትችት የአካዳሚክ ሕይወት የማይቀር አካል ቢሆንም፣ ከምሁራዊ አለመግባባት አልፎ ሄዷል።" ብለዋል።

"ያለማቋረጥ የሚሰነዘሩት ክሶች፣ ግምቶች እና የሕዝብ አስተያየቶች በእኔ እና በምወዳቸው ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።"

የሥራ መልቀቂያዬ "ከከበቡኝ ታሪኮች ጋር በተያያዘ ተቀባይነት እንዳለው ተደርጎ መታየት የለበትም" ሲሉም አፅንዖት ሰጥተዋል።

ኬምብሪጅ በመጀመሪያ ላይ ሊቨርፑል ጆን ሙርስ ዩኒቨርሲቲ (ኤልጄኤምዩ) እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ጆርናሎች፣ አርዴይ በምርምር ጽሑፉ (thesis) እና በአንዳንድ የታተሙ ጽሑፎቹ ውስጥ የሌሎችን ሰዎች ሥራ ኮርጆ ተጠቅሟል በሚል የቀረበውን ክስ መርምረዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 አርዴይን የዶክትሬት ዲግሪ የሰጠው ኤልጄኤምዩ ሥራውን ሰርቆ እንዳላቀረበ ደምድሟል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይም ኬምብሪጅ በሹመቱ ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንደሚደረግ አስታውቆ ነበር።