ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መስክ በትዊተር ኃላፊነቱ የመቀጠሉን ነገር በተጠቃሚዎች ድምጽ እንዲወሰን ጠየቀ
የትዊተር ባለቤት ኤለን መስክ የማህበራዊ ሚዲያው ተጠቃሚዎች በዋና ስራ አስፈጻሚነቱ በመቀጠሉ ዙሪያ ድምጽ እንዲሰጡ ጠይቋል።
122 ሚሊዮን ተከታዮቹ ባሉት የትዊተር ገጹ ባቀረበው የሕዝብ አስተያየት “ከትዊተር ኃላፊነቴ መልቀቅ አለብኝ? ይህን የሕዝብ አስተያየት ውጤት አከብራለሁ” ሲል ጽፏል።
እስከ ለመስክ ጠይቄ ከ13 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ድምጽ የሰጠ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 56በመቶ ከዋና ሥራ አስፈጻሚነቱ እንዲነሳ ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የድምጽ አሰጣጥ ከ4 ሰዓታት በኋላ ይጠናቀቃል።
ቴስላን እና ስፔስ ኤክስን የሚያስተዳድረው የቴክኖሎጂ ከበርቴ ትዊተርን ከገዛ በኋላ ከፍተኛ ትችት ገጥሞታል።
ከከፍተኛ ሕጋዊ ክርክር በኋላ መስክ በ44 ቢሊዮን ዶላር ነበር ኩባንያውን በጥቅምት ወር የጠቀለለው።
ይህ የሆነው ትዊተር ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ለማስተዋወቅ ብቻ የተከፈቱ አካውንቶችን እዘጋለሁ ካለ በኋላ ነው።
እርምጃው እንደ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ማስቶዶን፣ ትሩዝ ሶሻል፣ ትሪብል፣ ኖስትር እና ፖስት ካሉ ጋር የተገናኙ ወይም የእነሱን መለያዎችን የያዙትን ሊጨምር ይችላል ሲል ኩባንያው ገልጿል።
ከሌሎች ድረ-ገጾች የሚመጡ ይዘቶችን መለጠፍ ግን አሁንም ይፈቀዳል።
በቅርቡ በኖስትር ላይ መዋለ ንዋያቸውን ያፈሰሰው የቀድሞው የትዊተር አለቃ ጃክ ዶርሲ በትዊተር ገጹ ላይ “ለምን?” ሲል በአንድ ቃል ምላሽ ሰጥቷል።
ስለ ኖስትር እገዳ ጉዳይ ሌላ ተጠቃሚ በሰጠው ምላሽም ዶርሲ፣ "ትርጉም አልባ" ብሎታል።
ቅዳሜ ዕለት የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ቴይለር ሎሬንዝ አዲሱ ሕግ በይፋ ከመታወጁ በፊት በመግለጿ ታግዳለች።
እሑድ ዕለት እገዳው ከተነሳላት በኋላ በትዊተር ያሳገዳትን ጽሑፍ ድጋሚ ለጥፋለች።
መስክ ትዊተርን ከገዛ በኋላ ብዙ ተጠቃሚዎቹ ወደ ፈለሱበት ማስቶዶንን የሚያገናኘውን መስመር ከተጠቃሚዎቹ ከልክሎ ነበር።