ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ በዩክሬን ላይ አዲስ የሚሳኤል ጥቃቶችን ፈፀመች
ቅዳሜ ዕለት ሩሲያ በዩክሬን ላይ አዲስ የሚሳኤል ጥቃቶችን የፈፀመች ሲሆን በምሥራቃዊቷ ከተማ ድኒፕሮ በመኖሪያ ቤት ሕንጻ ላይ በደረሰው ጥቃት ቢያንስ 14 ሰዎች ተገድለዋል።
ኪዬቭን፣ ካርኪቭን እና ኦዴሳን ጨምሮ በርካታ ከተሞችም በጥቃቱ ዒላማ ሆነዋል።
የሚሳኤል ጥቃቱ በበርካታ ከተሞች የኃይል መሠረተ ልማትን ከመታ በኋላም ዩክሬን በአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ውስጥ ትገኛለች።
ቀደም ብሎ ዩናይትድ ኪንግደም የአገሪቷን የመከላከል አቅም ለመደገፍ "ቻሌንጀር 2" ታንኮችን ለዩክሬን እንደምትልክ አስታውቃ ነበር።
የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሹ ሱናክ "ቻሌንጀርስ" የእንግሊዝ ጦር ዋነኛው የውጊያ ታንክ እንደሆነ ገልጸው፣ ድጋፉ የኪዬቭ ኃይሎች የሩሲያን ወታደሮች ወደ ኋላ ለመግፋት ይረዳቸዋል ብለዋል።
ሩሲያ በበኩሏ ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎችን መስጠት ሩሲያ የምትወስደውን እርምጃና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ያባብሰዋል ብላለች።
ዩክሬናውያን የኦርቶዶክስን አዲስ ዓመትን በሚያከብሩበት ቅዳሜ ዕለት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ፣ "ሩሲያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የምትፈፅመው ጥቃት የሚቆመው የዩክሬን ምዕራባውያን አጋሮች አስፈላጊውን መሣሪያ ሲያቀርቡ ብቻ ነው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት “ለዚህ የሚያስፈልገው አጋሮቻችን መጋዘኖች ውስጥ ያሉት እና ወታደሮቻችን እየጠበቁ ያሉት የጦር መሣሪያዎች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
ጦራቸው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከተኮሰቻቸው 30 ሚሳይሎች ውስጥ ከ20 በላይ የሚሆኑትን መትተው እንደጣሉም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።
በዩክሬን ምሥራቃዊ ከተማዋ ዲኒፕሮ የደረሰው የሚሳኤል ጥቃት አንድ ሕንጻን የመታ ሲሆን በርካታ ክፍሎቹን ወደ ፍርስራሽ በመቀየር 14 ሕጻናትን ጨምሮ 73 ሰዎችን ለጉዳት ዳርጓል።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ጥቃቱ በወራት ውስጥ ከተፈፀመው አስከፊው ነው ብለዋል።
ጥቃቱ በተፈፀመበት ቦታ ላይ የነፍስ አድኑን ሥራ ለማየት በርካታ ሕዝብ የተሰባሰበ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የተረፉ ሰዎችን ለመፈለግ የነፍስ አድን ሠራተኞችን ተቀላቅለዋል።
አስቸኳይ ጥሪዎች፣ ፍርስራሾቹን የሚያጸዱ በርካታ ሰዎች የነበሩ ሲሆን አቧራ እና ጭስ ይታይ ነበር።
ዜሌንስኪ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክታቸው በዲኒፕሮ ፍርስራሽ የማጽዳት ሥራው ምሽቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
“ለእያንዳንዱ ሰው፣ ለእያንዳንዱ ሕይወት እየታገልን ነው” ብለዋል።
እስካሁንም ከሕንጻው ውስጥ ስድስት ሕጻናትን ጨምሮ 38 ሰዎችን ሕይወት መታደግ መቻሉን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ሕንጻው ለምን የጥቃቱ ኢላማ እንደሆነ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት መረጃ ባይኖርም ሕንጻው የሚገኘው በአቅራቢያው ከሚገኝ የኃይል መሠረተ ልማት በተወሰነ ርቀት ላይ ነው።
ሩሲያ ከሁለት ሳምንት በፊት በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈፀሟ ይታወሳል።
ዜሌንስኪ በቅዳሜ ዕለት ጥቃቱ የኃይል መሠረተ ልማት መመታቱን የገለጹ ሲሆን በካርኪቭ እና ኪዬቭ ግዛቶች ችግር ፈጥሯል።
የዩክሬን መንግሥት የኢነርጂ ድርጅት የሆነው ዩክሬኔርጎ ቀደም ብሎ በሁሉም ክልሎች በአገሪቷ ሰዓት አቆጣጠር እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የፍጆታ ገደብ መደረጉን አስታውቋል።
የምዕራቡ ዓለምና የዩክሬን ባለሥልጣናት በተስማሚ የሚሳይል እጥረትና ተደጋጋሚ ጥቃቱ የዩክሬንን መንፈስ ያልሰበረ በመሆኑ የሩሲያ የኢነርጂ ጦርነት ሊያከትም ይችላል ብለው ማሰብ ጀምረዋል።
ይሁን እንጂ የቅዳሜ ዕለቱ ጥቃት ሞስኮ አሁንም ልትከተለው የሚገባ ስልት እንደሆነ እንደምታስብ አመላክቷል።