ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ለወራት ውጊያ ሲደረግባት የነበረችውን ወሳኝ ከተማን ሶሌዳርን ተቆጣጠርኩ አለች
ለወራት ከዘለቀ ውጊያ በኋላ ሩሲያ ወታደሮቿ የጨው ማዕድን ማውጫ የሆነችውን የዩክሬን ከተማ ሶሌዳርን መቆጣጠራቸውን አስታወቀች።
ይህ ድል በዩክሬን ኃይሎች ላይ ለምታካሂደው ጥቃት “ወሳኝ እርምጃ ነው” ስትል ሩሲያ ያገኘችውን ድል ገልጻዋለች።
ከተማዋን ሠራዊቷ በቁጥጥሩ ስር ማስገባቱ በቅርበት ባለችው ትልቅ ከተማ ባኽሙት ውስጥ ላለው የዩክሬን ጦር የሚደርሰውን የአቅርቦት መስመር ለመቁረጥ ያስችላል ሲል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ተናግሯል።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ግን ሶሌዳርን ለመቆጣጠር የሚካሄደው ጦርነት እንደቀጠለ እና የሩሲያ መግለጫ “ጩኽት ለመፍጠር” ያለመ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ከተማዋን ለመቆጣጠር ለወራት የተካሄደው ውጊያ በሩሲያ እና በዩክሬን ኃይሎች መካከል ከተካሄዱት ደም አፋሳሽ ውጊያዎች መካከል አንዱ ነው።
የክልሉ አስተዳዳሪ ፓቭሎ ኪሪሌንኮ ሐሙስ ዕለት እንደተናገሩት በከተማዋ ውስጥ መውጣት ያልቻሉ 15 ልጆችን ጨምሮ 559 ሰላማዊ ሰዎች ይገኛሉ።
ሶሌዳር ከተማ በአንጻራዊነት ትንሽ በመሆኗ ለሩሲያ ሠራዊት ያላት ጠቀሜታ እስከዚህም ነው ሲሉ ወታደራዊ ተንታኞች ይናገራሉ። ነገር ግን ባለፉት 10 ወራት በጦርነቱ ፈተና ለገጠማት ሩሲያ እንደ ታላቅ ድል ሊታይ ይችላል።
በጦርነቶች ላይ ጥናት የሚያካሂደው የአሜሪካ ተቋም ከሰዓታት በፊት የሩሲያ ኃይሎች ሶሌዳርን ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ ጠቅሶ፣ ነገር ግን ትልቋን የባኽሙት ከተማን ለመክበብ ይችላሉ ብሎ እንደማያምን ገልጿል።
የዩክሬን ምሥራቃዊ ወታደራዊ ዕዝ ቃል አቀባይ እንዳሉት ሩሲያ ምርጥ የሚባሉ ቅጥረኛ ተዋጊዎቿን እና ሌሎች የጦር ቡድኖችን ወደ ሶሌዳር አሰማርታለች።
የዩክሬን ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ሃና ማለያር ሌሊቱን በሙሉ ከባድ ውጊያ ሶሌዳር ውስጥ ሲካሄድ እንደነበር ገልጸዋል።
ጨምረውም ውጊያው አስቸጋሪ በሆነበት ወቅት የዩክሬን ተዋጊዎችም “በጀግንነት መከላከያቸውን ላለማስደፈር ሲሞክሩ ነበር” ብለዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ትናንት ምሽት ባደረጉት ንግግር በሶሌዳር፣ በባኽሙት እና በምሥራቃዊ ዩክሬን የዶኔትስክ አካባቢ የሚደረገው የመከላከል ውጊያ ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው ነበር።