ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬን ወታደሮች በአሜሪካ የዘመናዊ አየር መቃወሚያ ሚሳኤል ሥልጠና ሊሰጣቸው ነው
የዩክሬን ወታደሮች በአሜሪካዋ ግዛት ኦክላሆማ የፓትሪዮት ሚሳኤል ሥርዓት ሥልጠና ሊሰጣቸው መሆኑን የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ፓትሪዮት ሚሳኤል ሥርዓት ከመሬት ወደ አየር የሚተኮስ ሲሆን ባልስቲክ ሚሳይሎችንና የጦር አውሮፕላኖችን ለመቋቋም የሚያስችል የአየር ጥቃት መከላከያ ዘዴ ነው።
የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታጎን እንዳስታወቀው እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ ከ90 እስከ100 የሚደርሱ ወታደሮች ከዩክሬን ወደ አሜሪካ የጦር ሠፈር ፎርት ሲል ይደርሳሉ።
የአሜሪካ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን የሚያንቀሳቅሱ ወታደሮች ሥልጠና በሚወስዱበት ፎርት ሲል የሚሰጠው ሥልጠና በርካታ ወራትን ይወስዳል ተብሎም ይጠበቃል።
ዩክሬን ዘመናዊ የሆነው የሚሳኤል ሚሳይል መቃወሚያ ሥርዓቱ ከሩሲያ ጋር የምታካሂደውን ጦርነት ይለውጠዋል ብላለች።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ፓት ራይደር በበኩላቸው “ፓትሪዮት ሚሳኤል የአየር ጥቃትን ለመከላከል አስተዋፅኦ ያደርጋል፤ በመሆኑም የዩክሬንን ሕዝብን ከሩሲያ የአየር ጥቃት ለመከላከል ተጨማሪ አቅም ይሰጣል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ባለፈው ወር የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በዋሽንግተን ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ ለዩክሬን የፓትሪዮት ሚሳኤል ባትሪ እንደምትሰጥ አስታውቀው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቨሥርዓቱን "ዘመን ያለፈበት" ሲሉ የተሳለቁ ሲሆን የሩሲያ ጦር የዩክሬን መከላከያን እንደሚያንበረክክ ዝተዋል።
ፓትሪዮት ሚሳኤል እንደ ክሩዝ ሚሳይሎች ያሉ ፈጣን የአየር ላይ ኢላማዎችን ማጥፋት የሚችል ከምድር ወደ አየር የሚተኩስ ሥርዓት ነው።
አንዱ ባትሪው የአንድ ዓመት ሥልጠና በወሰዱ 90 ወታደሮች የሚንቀሳቀስ ነው።
የዩክሬን ወታደሮች በዚህ ላይ የተፋጠና ሥልጠና የሚያገኙ ሲሆን ሥልጠናውን ለማጠናቀቅ ግን ብዙ ወራትን ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ሥልጠናው በክፍል ውስጥ የሚሰጡ እና በቤተሙከራ የሚካሄዱ ተግባራዊ ትምህርቶችን ያካትታል።
ባለፈው ሳምንት ጀርመን ለዩክሬን ፓትሪዮት የሚሳኤል ሥርዓት እንደምትሰጥ አስታውቃለች።
ከዚህም በተጨማሪ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን እንደምትሰጥ የገለጸች ሲሆን ፈረንሳይ በበኩሏ ቀላል ታንኮችን እንደምትልክ ቃል ገብታለች።
አሜሪካ የፓትሪዮት ሚሳኤል ሥልጠና ለዩክሬን እንደምትሰጥ ያስታወቀችው ፕሬዝዳንት ባይደን በሜክሲኮ በሚካሄደው ጉባኤ የካናዳ እና የሜክሲኮ መሪዎች ጋር ከተገናኙ በኋላ ነው።
ማክሰኞ ዕለት የካናዳ ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ አገሪቷ አሜሪካ ሰራሹን መካከለኛ ርቀት መጓዝ የሚችል ዘመናዊ ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፍ ሚሳኤል ( ናሳም) ለዩክሬን እንደምትገዛ አስታውቀዋል።
የካናዳ መከላከያ ሚኒስተር አኒታ አናንድ “ይህ ካናዳ ለዩክሬን የአየር መቃዋሚያ ድጋፍ ስትሰጥ የመጀመሪያዋ ነው” ሲሉ በትዊትረ ገጻቸው አስፍረዋል።
ይህ አጭር እና መካከለኛ ርቀት የሚጓዘው ከምድር ወደ አየር የሚተኮሰው ሚሳኤል ካናዳን 300 ሚሊየን ዶላር ያስወጣታል።
ካናዳ ከዚህ ቀደም ኅዳር ላይ የ500 ሚሊየን የካናዳ ዶላር ድጋፍ ለዩክሬን ለመስጠት ቃል መግባቷ ይታወሳል።
በዓለም ላይ እጅግ ዘመናዊና የላቀ አየር መቃወሚያ ተደርጎ የሚታሰበው ፓትሪዮት ሚሳኤል ሥርዓት፣ አንድ ባትሪው ብቻ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ያስወጣል።