ጥቁር አሜሪካዊው የአየር ኃይል አባል በመኖሪያ ቤቱ በፖሊስ ተገደለ

ታትሟል

ጥቁር አሜሪካዊው የአየር ኃይል አባል በመኖሪያ ቤቱ ከፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን የሚያሳይ ቪዲዮ የፍሎሪዳ ፖሊስ ለህዝብ ይፋ አደረገ።

ቪዲዮው በጥይት ከተኮሰበት ፖሊስ ከተገጠመ የሰውነት ካሜራ የተገኘ ነው።

የ23 ዓመቱ የአየር ኃይል አባል ሮጀር ፎርትሰን ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ህይወቱ ማለፉን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

የተገዳዩ ቤተሰቦች ጠበቃ ምስክሮችን ዋቢ አድርገው ፖሊስ የተሳሳተ ቤት መግባቱን ተናግረዋል።

ፖሊስ በበኩሉ ይህንን አስተባብሎ የአየር ኃይል አባሉ መሳሪያ መታጠቁን ካየ በኋላ ራሱን ለመከላከል ያደረገው ምላሽ ነው ብሏል።

የአየር ኃይል አባሉ በተሰማራበት ፍሎሪዳ ከሚኘው ኸርልበርት ፊልድ የጦር ሰፈር በቅርብ ርቀት በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ከሳምንት በፊት ነው በጥይት ተመትቶ የተገደለው።

የአየር ኃይሉን በጥይት መትቶ የገደለው እና ፖሊስ ስሙን ይፋ ያላደረገው ፖሊስ በፍቃድ ከስራው እንዲገለል ተደርጓል።

የኦካሎሳ ግዛት ፐሊስ ኃላፊ ኤሪክ አደን እንደተናገሩት ግድያው በፍሎሪዳ የህግ ማስከበር ማዕከል እና የግዛቲቱ ዓቃቤ ህግ ቢሮ እየመረመሩት ነው። ኃ

ላፊው “ግልጽነት እና ተጠያቂነት” ያለው ምላሽ ለመስጠት ቃል ገብተው ነገር ግን “እነዚህ ምርመራዎች ጊዜ ይወስዳሉ” ብለዋል።

“ነገር ግን ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው በሟቹ ሮጀርም ሆነ በፖሊሱ ላይ አፋጣኝ ፍርድ የሚያስከትል መደበቅ፣ መሸፋፈን ወይም ማንኛውንም እርምጃ አንወስድም” ብለዋል።

የአየር ኃይሉን አባል ተኩሶ ሲገድለው የሚያሳየው የአራት ደቂቃ ቪዲዮ ክስተቱን አሳይቷል። ፖሊስ የአየር ኃይል አባሉ የሚኖርበት ህንጻ ደርሶ ጸብ ሰምቻለሁ ባሉ ምስክር ወደ አሳንሰሩ ሲያመራ ያሳያል።

ፖሊስ የመኖሪያ ቤቱ በር ላይ ደርሶ በሩን ሲያንኳኳ እና ፖሊስ መሆኑን ሲናገር ይሰማል።

የአየር ኃይል አባሉ ሽጉጥ ይዞ በሩን ሲከፍት ይታያል፤ ልክ በሩ እንደተከፈተ ፖሊስ በርካታ ጥይቶች ከተኮሰበት በኋላ መሳሪያውን እንዲጥል ነግሮታል። መሬት ላይ የወደቀው የአየር ኃይል አባል “መሳሪያ አልያዝኩም ፤ እዚያ ነው ያለው” ሲል ይሰማል።

የአየር ኃይል አባሉ የቤተሰብ ጠበቃ ቤን ክረምፕ በነበራቸው መግለጫ “አሜሪካ የነበራት ምርጥ ሰው ነበር። ጀግና፣ አገር ወዳድ ነበር። ለህይወታችን፣ ለሁላችንም እየተዋጋ” ነበር ብለዋል።

የአየር ኃይል አባሉ እናት ቻንቲሜኪ ፎርትሰን በበኩላቸው “ልጄ ሁሉ ነገሬ ነበር” ሲሉ በከፍተኛ ሁኔታ እያለቀሱ ተናግረዋል።

ጠበቃው እንደገለጹት የአየር ኃይል አባሉ በተተኮሰበት ወቅት ከጓደኛው ጋር በቪዲዮ እያወራ የነበረ ሲሆን እሷም በወቅቱ የሰማችውን ለቤተሰቡ መግለጿን ተናግረዋል።

በሩ ሲንኳኳ ማን ነው ቢልም ምላሽ እንዳላገኘና በሁለተኛው በኃይል ሲንኳኳ በበሩ ቀዳዳ ሲመለከት ማንንም ማየት እንዳልቻለ ነው።

በሁኔታው በጣም የሰጋው የአየር ኃይል አባል ሽጉጡን ሊያመጣ ሲሄድ በሩን በርግዶ የገባው ፖሊስ ስድስት ጊዜ ተኩሶ እንደገደለው ምስክሩ ተናግረዋል። ጠበቃው ሮጀር በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ብቻውን እንደነበረ እና ረብሻ ተከስቶበታል የተባለው ቤት ባለመሆኑ ፖሊሶች ተሳስተው እንደገቡ ገልጸዋል።