ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ የጂቡቲ ወታደሮችን ማስለቀቁን የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ
በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ ስድስት የጂቡቲ ወታደሮችን አስለቅቆ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ወታደሮቹ ፍሩድ (ዘ ፍሮንት ፎር ዘ ሪስቶሬሽን ኦፍ ዩኒቲ ኤንድ ዲሞክራሲ) በተሰኙ የጂቡቲ ታጣቂዎች ታግተው እንደነበርም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረቡዕ ታኅሣሥ 12/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮቹን ከታጣቂዎቹ እገታ ማስለቀቅ የቻለው በተቀናጀ ስለላ እና የፖሊስ ዘመቻ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፍስሐ ሻወል መናገራቸው ሰፍሯል።
ወታደሮቹን በማስለቀቅ ሂደት የማኅበረሰቡ አመራሮች እና የአፋር ክልል አስተዳደር ከፍተኛ ሚና መጫወቱ ቢገለጽም ወታደሮቹ በየትኛው ስፍራ ታግተው እንደነበር አልተገለጸም።
ከእገታ የተለቁትን ወታደሮች ለጂቡቲ መንግሥት ማስረከባቸውን እና በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያለውን ትብብርን አጽንኦት መሰጠቱንም አምባሳደሩን ዋቢ አድርጎ መግለጫው አመላክቷል።
የታጣቂ ቡድኑ ፍሩድ መስከረም 26/2015 ዓ.ም. ጂቡቲ ታድጁራ ክልል ውስጥ በሚገኘው ጋራብቲሳን የጦር ሰፈር ጥቃት ካደረሱ በኋላ ወታደሮቹ መታገታቸው ተገልጿል።
በጋራብቲሳን ጦር ሰፈር በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ ሰባት ወታደሮች ሕይወታቸውን እንዳጡና ተጠያቂውም “የአሸባሪ ቡድን” የተባለው ፍሩድ ነው ሲል የጂቡቲ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።
በዚሁም መግለጫ ላይ ከሞቱት በተጨማሪ አራት ወታደሮች መቁሰላቸው እና ስድስቱ መጥፋታቸው ተገልጿል።
ፍሩድ በበኩሉ ከጦር ሰፈሩ አስራ አምስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ስፍራ የጂቡቲ ጦር ላደረሰበት ጥቃት ምላሽ እንደሆነም መግለጹ ተዘግቧል።
ፍሩድ ታጣቂዎቹ የጦር ሰፈሩን ተቆጣጥረው መቆየታቸውን እና መሳሪያ እና ጥይቶችም መውሰዳቸውን ቢገልጹም የጂቡቲ ባለሥልጣናት ግን ውድቅ የቡድኑን የጦር መሳሪያ ምርኮ ጉዳይ ውድቅ አድርጎታል።
ይህንንም ጥቃት ተከትሎ የጂቡቲ ፓርላማ ቡድኑን በአሸባሪነት ፈርጆታል።
ቡድኑ በጂቡቲ ጦር ሰፈር ላይ የፈጸመውንም ጥቃት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) እና የጅቡቲ ዋና የንግድ አጋር የሆነችውን ኢትዮጵያን ጨምሮ ክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አውግዘውታል።
በአውሮፓውያኑ 1991 የተቋቋመው ፍሩድ በጂቡቲ መንግሥታዊ ሥርዓት መገለል ደርሰቦቸዋል የሚለውን የአፋር ሕዝብ ጥያቄን ይዞ የተነሳ እንደሆነ ይነገራል።
ከበርካታ ውጣ ውረዶች በኋላ በአውሮፓውያኑ 2001 ፍሩድ ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራርሞ ነበር።
ነገር ግን የታጣቂው ክንፍ ስምምነቱን ውድቅ በማድረግ በትጥቅ ትግሉ እቀጥላለሁ ያለ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜም ይህ ነው የማይባል ጉልህ ወታደራዊ እርምጃ ሳይወስድ ቆይቷል።