ጀርመን የመጤ ጠል ጽንፈኞችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ጠንካራ እርምጃዎች ይፋ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጀርመን መንግሥት በአገሪቱ እየተጠናከረ የመጣውን መጤ ጠል የቀኝ ክንፍ ጽንፈኞችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችለውን የሕግ ማዕቀፍ ይፋ አደረገ።
መንግሥት ይህንን እርምጃ የወሰደው በተለያዩ የጀርመን ከተሞ የቀኝ ክንፍ እንቅስቃሴዎችን የሚቃወሙ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎት ለሳምንታት ከተካሄዱ በኋላ ነው።
ባለፈው ጥር ወር ብቻ በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ የተሰማሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጀርመናውያን የቀኝ ክንፍ ጽንፈኞችን በመቃወም ወደ ጎዳናዎች ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌሰር በአገሪቱ የተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች መንግሥታቸው ፖለቲካዊ እርምጃ እንዲወስድ “ማበረታቻ እና ይሁንታን” እንደሰጠው ገልጸዋል።
ኤኤፍዲ የተባለው ፓርቲ ከፍተኛ አባላት እና የኒዮ-ናዚ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች የውጭ አገር ዜጎችን በጅምላ ከጀርመን ስለማባረር ባለፈው ወር ላይ “በምሥጢር” ስለመወያየታቸው ይፋ መሆኑ በአገሪቱ ድንጋጤን ፈጥሯል።
“ዴሞክራሲያችንን ለመጠበቅ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚየስችሉ ሁሉንም መሳሪያዎች መጠቀም እንፈልጋለን” ሲሉ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፌሰር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“የቀኝ ክንፍ ጽንፈኞችን መረብ መበጣጠስ፣ የገንዘብ ምንጫቸውን ማቋረጥ እና የታጠቋቸውን የጦር መሳሪያዎች ማስፈታት እንፈልጋለን” ብለዋል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት 13 ነጥቦችን ያየዘው የሕግ ማዕቀፍ ለጀርመን ማኅበረሰብን ታላቅ ስጋት ሆኖ የቀረቡትን የቀኝ ክንፍ ጽንፈኞችን ለመዋጋት አስፈላጊ ነው።
በሕግ ማዕቀፉ ውስጥ የጽንፈኞቹን የባንክ አካውት እና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ለማገድ አዲስ ሕግ እንዲወጣ ሃሳብ ተካቷል። በተጨማሪም ለእነዚህ ቡድኖች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉትም ዒላማ ይደረጋሉ።
እንቅስቃሴያቸውን ለመቆጣጠር በወጣው ሕግ ባለሥልጣናት ጽንፈኛ ቡድኖቹ የሚያዘጋጇቸውን መረሃ ግብሮችን በቀላሉ ለመከልከል እና የቡድኑ አንቀሳቃሾችም ከአገር እንዳይወጡ እና እንዳይገቡ በቀላሉ ለመከልከል የሚያስችል ሥልጣን ይሰጣል።
የጦር መሳሪያ ባለቤትነትን የተመለከተው የአገሪቱ ሕግም የሚጠብቅ ሲሆን፣ በጽንፈኝነት ተከሰው ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ የመንግሥት ሠራተኞችም በቀላሉ ከሥራ የሚባረሩ ይሆናል።
የፀረ ዘረኝነት እንቅስቃሴ ቡድኖች የጀርመን መንግሥት በቀኝ ክንፍ ጽንፈኞች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ መነሳቱን በበጎ የተመለከቱት ቢሆንም፣ የእንቅስቃሴውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ግን እርምጃው የዘገየ ሊሆን ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ተመሳሳይ የሕግ ረቂቅ ቀደም ሲል ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ በአገሪቱ ምክር ቤት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። አሁን ግን በቀኝ ክንፍ ጽንፈኞች ላይ ሕዝቡ እያሰማ ባለው ተቃውሞ ምክንያት አሁን የቀረበው የሕግ ማዕቀፍ ብዙም ተግዳሮት አይገጥመውም ተብሏል።
የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚለው በዓመት ውስጥ 20 ሺህ የሚደርሱ የቀኝ አክራሪዎች ወንጀል እና ጥቃቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ እንዲህ አይነቶቹ ክስተቶችም እየጨመሩ ናቸው።
የአገሪቱ የደኅንነት አገልግሎት መረጃ እንደሚያመለክተው ከ38,000 ሺህ በላይ ጀርመናውያን የቀኝ ክንፍ ጽንፈኛ ናቸው ተብለው የሚታወቁ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም 14,000 የሚሆኑት አደገኛ ናቸው ተብለው ተለይተዋል።
ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ በቀኝ ክንፍ ጽንፈኞች ላይ ቢሰማም ከእንቅስቃሴው ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት ኤኤፍዲ የተባለው ፓርቲ በቅርቡ በተካሄደ ምርጫ ያገኘው ድምጽ ጨምሯል።












