የአማዞን መሥራቹ ባለሀብት ጄፍ ቤዞስ ከድርጅቱ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ አክሲዮን ሸጠ

ጄፍ ቤዞስና የፍቅር ጓደኛው ሎረን ሳንቼዝ [በስተግራ]

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄፍ ቤዞስና የፍቅር ጓደኛው ሎረን ሳንቼዝ [በስተግራ]
ታትሟል

ቢሊየነሩ ጄፍ ቤዞስ አማዞን ከተሰኘው ድርጅቱ አክሲዮን 4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚሆነውን በቅርቡ መሸጡ ተሰምቷል።

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አማዞን የተመሠረተው በአውሮፓውያኑ 1994 ነው።

ኩባንያው ባለንበት ወርሃ የካቲት ቢሊየነሩ የድርጅቱ መሥራች 24 ሚሊዮን የድርጅቱን ድርሻ መሸጡን ይፋ አድርጓል።

የኩባንያው ሊቀ-መንበር የሆነው ቤዞስ ለመጨረሻው ጊዜ ከድርጅቱ ድርሻ ቆንጥሮ የሸጠው በአውሮፓውያኑ 2021 ነበር።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኩባንያው ጉምቱው ቱጃር ከድርጅቱ አክሲዮን 50 ሚሊዮን የሚሆነውን ለገበያ ለማቅረብ እንዳቀዱ አስታውቋል።

ይህ የአክሲዮን መጠን በገንዘብ ሲሰላ 8.4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይሆናል።

የመጀመሪያው 12 ሚሊዮን የአክሲዮን ድርሻ ለገበያ የቀረበው ባለፈው ሳምንት አርብ ሲሆን፣ ሁለተኛው 12 ሚሊዮን ደግሞ ማክሰኞ ዕለት ለገበያ መቅረቡ ተሰምቷል።

ቤዞስ፤ ዋሺንግተን ግዛት ከምትገኘው ሲያትል ነቅሎ መኖሪያ አድራሻውን ወደ ፍሎሪዳ ግዛት ማያሚ ማድረጉን ባለፈው ዓመት ገልጾ ነበር።

ይህ ማለት ቢሊየነሩ ከሚያገኘው ገቢ ምንም ዓይነት ግብር ለመንግሥት አይከፍልም ማለት ነው።

ባለሀብቱ መኖሪያ አድራሻውን የቀየረው ዋሺንግተን ግዛት በርካታ አክሲዮን የሚሸጡ ሰዎች ላይ ግብር መጣሏን ተከትሎ ነው የሚሉ ጭምጭምታዎች ተሰምተው ነበር።

በዋሺንግተን ግዛት ሕግ መሠረት ከአክሲዮን ሽያጭ የሚገኘው ከ250 ሺህ ዶላር በላይ ከሆነ 7 በመቶ የሚሆነውን ለመንግሥት ማስገባት ግዴታ ነው።

ግዛቷ ከዚህ ሕግ መጽደቅ በኋላ ባለፈው ዓመት 900 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተሰምቷል።

ጄፍ ቤዞስ መኖሪያ አድራሻውን ባይቀይር ኖሮ ከሚያገኘው 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ 280 ሚሊዮን ዶላር ለመንግሥት ማስገባት ይጠበቅበት ነበር።

ቤዞስ ባለፈው ኅዳር ሲናገር ቤተሰቦቼ ወደ ማያሚ አቅንተዋል፤ ከእነሱ አጠገብ ለመሆነ ነው ሲል ለምን ከዋሺንግተን ነቅሎ እንደወጣ አስረድቷል።

ጄፍ ቤዞስ የተወሰነውን የልጅነቱን ዘመኑን ፍሎሪዳ ግዛት አሳልፏል።

ብሉ ኦሪጂን የተሰኘው የሕዋ ምርምር ተቋሙ መገኛም እዚያው ፍሎሪዳ ግዛት ነው።

“ሎረን እና እኔ ማያሚን በጣም ነው የምንወዳት” ሲል እጮኛው ሎረን ሳንቼዝም እንዲሁ ሥፍራውን እንደምትወደው ገልጿል።

ሀብቱ በገንዘብ ሲሰላ 190 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል የሚባልለት ጄፍ ቤዞስ፣ አሁንም የኩባንያው ትልቁ የአክሲዮን ባለድርሻ ነው።