በወልቂጤ ግድያ የፈጸሙ የፀጥታ ኃይሎች በሕግ ይጠየቁ በሚል ነዋሪዎች አድማ መቱ

የፎቶው ባለመብት, Wolkite FM
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የውሃ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ እና የውሃ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የተኮሱ የፀጥታ ኃይሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ በመጠየቅ ከቤት ያለመውጣት አድማ መምታታቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከቤት ያለመውጣት አድማው ከተጀመረ ቀናት መቆጠራቸውን የተናገሩት ነዋሪዎች የከተማዋ እንቅስቃሴም ሙሉ በሙሉ ተገድቧል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በከተማዋ ለወራት የተቋረጠው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ለመጠየቅ ባለፈው ሳምንት ጄሪካን ይዘው አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን እና ቢያንስ 30 ሰዎች የአካል ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች እና ኢሰመኮ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
በከተማዋ ትራንስፖርት፣ የባንክ አገልግሎት፣ የመገበያያ መደብሮችም ሆነ የትኞቹም የመንግሥት ተቋማት ተዘግተው ከተማዋ ጭር ብላ መሰንበቷን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ሰኞ ምሽት ገልጸዋል።
ሰልፈኞች ከተገደሉ በኋላ በተጀመረው ከቤት ያለመውጣት አድማ ሦስቱን ሰዎች ተኩሰው የገደሉ የፀጥታ ኃይል አባላት በሕግ እንዲጠየቁ፣ “ውሃ የጠማው ሕዝብ ውሃ እንዲሰጠው” ለመጠየቅም ሕዝቡ በራሱ ተሰባስቦ የጠራው አድማ ነው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠየቀስ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል።
“ሕረተሰቡ በራሱ ፈቃድ ነው ቤት የተቀመጠው። አድማ የጠራ አካል የለም። የሕብረተሰቡ ጥያቄ አንድ እና አንድ ውሃ እና መሠረተ ልማቶች ይመለሱልን ነው” የሚል ነው ብለዋል ነዋሪው።
የውሃ አቅርቦት ችግር ለዓመታት የዘለቀ መሠረታዊ ችግር እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪው በአሁኑ ወቅት ደግሞ “ሕዝቡ ውሃ መጠማቱን እየተናገረ ነው” ብለዋል።
ሌላኛው ነዋሪም አድማ የጠራ፣ ወረቀት የበተነ አካል እንደሌለ ገልጸው፣ ውሃ ጠማን ያሉ ነዋሪዎች መገደላቸው በሕብረተሰቡ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል ብለዋል።
ከሞቱት በተጨማሪ ከዚህ ሰልፍ ጋር ተያይዞ የታሰሩ እና እስካሁን ያልተፈቱ ሰዎች እንዳሉ የገለጹት ነዋሪዎች መንግሥት ይህንን አስመልክቶ ያለው ነገር የለም ብለዋል።
“የሞቱት ፍትህ ሊያገኙ ይገባል” በሚል ጥያቄያቸውን ከቤት ባለመውጣት እያሰሙ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ካለፈው ሳምንት አጋማሽ በኋላ በከተማዋ ፍተሻ እና እስሮች እንዳሉ ነዋሩዎች ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፣ በእስሩም የጉራጌ ክልልነት ጥያቄ እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበሩ ሰዎች ኢላማ መሆናቸውንም ነው ነዋሪው የተናገሩት።
በከተማዋ ውስጥ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴ እንደጀመር የፀጥታ ኃይሎች እና የአስተዳደር ባለሥልጣናት እየተዘዋወሩ ግፊት እያደረጉ እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በወልቂጤ የተጀመረው ከቤት ያለመውጣት የሥራ ማቆም አድማ ወደ አጎራባች አንዳንድ አካባቢዎች መዛመቱንም ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የክልሉም ሆነ የዞኑ መስተዳደር ነዋሪዎች አድማ እንዲመቱ ስላደረጋቸው ጥያቄ አስካሁን በይፋ የሰጡት ምላሽ የለም።
ከሰሞኑ በሰልፈኞች ላይ የተከፈተውንም ተኩስ በተመለከተ እናት ፓርቲ የካቲት 13/2015 ዓ.ም. በማውገዝ መግለጫ ሰጥቷል።
“የክልሉ የፀጥታ ኃይል ፍጹም ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ውሃ ጠምቷቸው የወጡ ዜጎችን ገድሏል፣ ደብድቧል፣ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ለከፍተኛ እንግልት እና ስቃይ ዳርጓቸዋል” ብሏል።
ከዚህ ቀደም በዞኑ እና በከተማው ማኅበረሰብ የክልልነት ጥያቄ ተነስቶ የእስር እና የወከባ ምላሽ መሰጠቱን ያስታወሰው መግለጫው፣ በቅርቡ የተከሰተውም ተመሳሳይ ነው ሲል ፈርጆታል።
“አሁንም ከዚያው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ቂምን መወጣት በሚመስል መልኩ ባዶ ጄሪካን ይዛ የወጣችን እናት የኃይል አማራጭ ተጠቅሞ የውሃ ጥም ጥያቄያቸውን በመግደል ለማርካት መሞከር የጭካኔ ጥግ ይመስለናል” ብሏል ፓርቲው።
በዚህም ፓርቲው በመግለጫው እንደ መፍትሄ ያቀረበው የከተማው ነዋሪው የውሃ ጥያቄ መሠረታዊ፣ ፍትሃዊ እና አጣዳፊ በመሆኑ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም “ጥያቄያቸውን እና ቅሬታቸውን በሰላማዊ መንገድ እየገለጹ የነበሩ ንጹሃንን በጭካኔ የገደሉ እና ያንገላቱ የፀጥታ አካላት በአፋጣኝ ለፍርድ እንዲቀርቡ” ጠይቋል።
ለአደባባይ ተቃውሞ ከወጡ ሰልፈኞች ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ክስተት ተቋማት በተገቢው መልኩ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ እና በተፈጠረው የፀጥታ ሥጋት የነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በእጅጉ መገተታቱንም መግለጫው ጠቅሷል።
መንግሥት ይህንን ጉዳይ ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ በዞኑ የተስተጓጎለው የዜጎች ሰላማዊ እንቅሰቃሴ ወደነበረበት እንዲመለስ እንዲደረግም ጠይቋል።
በከተማዋ የቧንቧ ውሃ አቅርቦት ከወር በላይ ለሆነ ጊዜ በመቋረጡ መንግሥት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ ፖሊስ በከፈተው ተኩስ የተገደሉት ሦስት ሰዎች ጭንቅላታቸው እና ደረታቸውን በጥይት ተመትተው መሆኑን ኢሰመኮ ማስታወቁ ይታወሳል።
ኮሚሽኑ የፀጥታ ኃይሎች በሰልፈኞቹ ላይ በወሰዱት ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ ለደረሰው የሕይወት መጥፋት እና የአካል ጉዳትም ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባም ኢሰመኮ አርብ የካቲት 10/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።
“አንገብጋቢ በሆነ የውሃ አቅርቦት ጥያቄ ሰልፍ ወጥተው ድንጋይ በወረወሩ እና መንገድ በዘጉ ሰዎች ላይ ሕይወት የሚያጠፋ መሣሪያ ተጠቅሞ እና ጥይት ተተኩሶ ነዋሪዎች መገደላቸው ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ ነው” የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል።
ጨምረውም የክልሉ መንግሥት አስቸኳይ ማጣራት አድርጎ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እና የተጎዱ ሰዎችም ተገቢውን ካሳ ሊያገኙ ይገባል በማለት አሳስበዋል።
ኮሚሽነር ዳንኤል ለወደፊቱም ተመሳሳይ ዓይነት የመብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለፀጥታ ኃይሎች ግልጽ አመራር መሰጠት አለበት ሲሉ መምከራቸውን መግለጫው አስፍሯል።












